Popular Posts

Saturday, February 24, 2018

እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል

እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5-6
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ያዕቆብ 4፡6-7
እግዚአብሄር የትሁታን ቡድን አባል ነው፡፡ እግዚአብሄር ትሁታንን ይደግፋል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኞችን ይቃወማል፡፡
እግዚአብሄር ትእቢትን ለምንድነው የሚቃወመው የሚለውን ለመረዳት ትእቢት ምን እንደሆነ እንመልከት
ትእቢት
1.      እኔ ብቻ አውቃለሁ ማለት ነው፡፡
ትእቢተኛ ሰው ከሰው ሁሉ በላይ የሚያውቅ ይመስለዋል፡፡ በትእቢተኛ ሰው ቤት ሌላው ሁሉ ሞኝ እርሱ ብቻ ብልጥ የሆነ ይመስለዋል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ያለው ትንሽ እውቀት የእውቀት ሁሉ ጣራ ይመስለዋል፡፡
እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1 ቆሮንቶስ 8፡1-2
2.     እኔ እችላለሁ ማለት ነው
ትእቢተኛ ሰው የሚታወቀው እግዚአብሄር ያስችለኛል ሳይሆን እኔ እችላለሁ በማለቱ ነው፡፡ በአፉ እግዚአብሄር እግዚአብሄር ሊል ይችላል ነገር ግን በልቡ እኔም ቀላል ሰው አይደለሁም ይላል፡፡ ትእቢተኛ ሰው በራሱ ጉልበት ይታመናል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ለእግዚአብሄር የሚሰጠው ስፍራ የለም፡፡ ትእቢተኛ ሰው የሚፈልገውን ሁሉ ራሱ ያደርገዋል፡፡ ትእቢተኛ ሰው በእግዚአብሄር ለመደገፍ እና እግዚአብሄርን ለመጠበቅ ጊዜ የለውም፡፡  
ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሃንስ 15፡5
3.     ማንም አያስፈልገኝም ማለት ነው
ትእቢተኛ ሰው ማንም የማያስፈልገው እርሱ ብቻ በቂ እንደሆነ ያስባል፡፡ ትእቢተኛ ሰው የሚታወቀው እኔ እኔ እኔ በማለት ነው፡፡ እኛ የሆነውን የሆነው በብዙ የአካካቢያችን ሰዎች አስተዋፅኦ ቢሆንም ትእቢተኛ ሰው ግን የሚያስበው እርሱ በአካባቢው ላሉ ሰዎች ሁሉ ምሰሶ እንደሆነ እንጂ ማንም እንደማያስፈልገው ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ማንም እንደማያስፈልገው ከልቡ ያስባል፡፡
ጆሮም፦ እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 12፡16
4.     ተምሬ ጨርሻለሁ ማለት ነው
ትእቢተኛ ሰው የሚማር ልብ የለውም፡፡ ትእቢተኛ ሰው በእውቀት ላይ ይቀልዳል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ሌላውን ለመስማት ጆሮ የለውም፡፡ ትእቢተኛ ሰው ሌላውን መስማት መሸነፍ እጅ መስጠት አድርጎ ስለሚያስብ ሌላውን መስማት አይፈልግም፡፡ ትእቢተኛ ሰው መማር ስላቆመ መሞት ጀምሯል፡፡
እርሱም፦ የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ሐዋሪያት 8፡31
5.     ማንም አያዘኝም ማለት ነው
እያንዳንዱ ሰው በተለያየ የህይወት ክፍሉ የሚያዘው ሌላ ሰው አለ፡፡ እኛ ውስን ነን፡፡ የተሰጠን ሃላፊነት ውስን ነው፡፡ እኛ በሁሉም የህይታችን ክፍል ሰውን ሁሉ ልናዝ አንችልም፡፡ ሃላፊነት በተሰጠን የህይወት ክፍል የምናዝዝ ብንሆንም ሃላፊነት ባልተሰጠን የህይወት ክፍል ደግሞ ሃላፊነቱና ስልጣኑ ላላቸው ሰዎች እንታዘዛለን፡፡ ወደ አንድ ቢሮ ስንሄድ በዚያ ሃላፊነት ላለበት ሰው መታዘዝ ግዴታ ነው፡፡ በመንግስት ለተሾመው መታዘዝ ያስፈልጋል፡፡ በቤተክርስትያን የአገልግሎት ክፍል ስልጣን ላለው ሰው መታዘዝ አንድነትን ይጠብቃል፡፡ በመንገድ ስትሄድ ለመንገድ ስርአትና ለትራፊክ ፖሊስ መገዛት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ በህይወት ከምናዘው ይልቅ የምንታዘዘው ይበልጣል፡፡ እንዲያውም የማዘዝ መሰረቱና ስልጣኑ የሚመጣው ከመታዘዝ ነው፡፡ መታዘዝ የማያውቅ ሰው ማዘዝ አያውቅም፡፡ የሰው የማዘዝ ችሎታው የሚለካው ለስልጣን ባለው ግንዛቤና ለመታዘዝ ባለው ንቃት ነው፡፡ ለማዘዝ ብቁ የሚያደርገን መታዘዛችን ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5-6
6.     ማንም አይበልጠኝም ማለት ነው
እኛ የምንበልጥበት የተወሰነ የህይወት ክፍል አለ፡፡ ነገር ግን የምንበልጠው በዚያ ብቻ ነው፡፡ በሌላው የህይወት ክፍል የሚበልጡን አያሌዎ ናቸው፡፡ ትእቢተኛ ሰው በአንድ የህይወት ክፍል ስለበለጠ በሁሉም የህይወት ክፍል የሚበልጥ ይመስለዋል፡፡ በአንድ የህይወት ክፍል በመብለጡ በሁሉም የህይወት ክፍል ለመብለጥ ይፈልጋል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
7.     ከሁሉም ሰው በላይ አስፈላጊ ነኝ ማለት ነው  
ሰው ራሱን አስፈላጊ ማድረግ ትክክል ነው፡፡ ሰው ራሱን አስፈላጊ አለማድርግ በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአላማ ተፈጥሯል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለእግዚአብሄር ውድ ነው፡፡ ትእቢተኛ ራሱን ብቻ አስፈላጊ ሌሎችን አላስፈላጊ አድርጎ ያስባል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ራሱ ብቻ የተመረቀ ከፍተኛ ኮከብ /ሱፐር ስታር/ ተደርጎ የተሰራ ሌሎቹ ሁሉ ደግሞ እርሱን ለማኗኗር የተፈጠሩ አድርጎ ያስባል፡፡
8.     መጀመሪያ ልሁን ማለት ነው
ትእቢተኛ ሰው ስልጣንን እንደ መጠቀሚያ እንጂ እንደ ማገልገያ መንገድ አያየውም፡፡ ሃላፊነቱንና ሸክሙን የሚረዱ ሰዎች ለስልጣን ያን ያህል አይጓጉም፡፡ ሰው ለስልጣን በጣም የሚጓጓ ከሆነ ከሃላፊነቱ ይልቅ የሳበው ጥቅሙ ነው ማለት ነው፡፡ ትእቢተኛ ስወ ሁሌ አንደኛ መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ ትእቢተኛ ስው ለማገልግል ሳይሆን ለመጠቀም አንደኛነቱን ይፈልገዋል፡፡ ከሆነ   
ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ፦ ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው። ማርቆስ 9፡35
9.     ምንም አይመጥነኝም ማለት ነው
ትእቢተኛ ስው ምንም አይነት ደረጃ ብትሰጡት ራሱን ከሰቀለበት ደረጃ አንፃር ምንም አይመጥነውም፡፡ ምንም ነገር ለእርሱ በቂ አይደለም፡፡ ያለኝ ይበቃኛል የሚል ነገር አታዩበትም፡፡ ምንም ብታደርጉለት ለራሱ ከሰጠው ቦታ አንፃር ምንም አይበቃል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ክብር አይበቃውም፡፡ ትእቢተኛ የሚመጥነው ሰው የለም፡፡ ትእቢተኛ ሰው የሚመጥነው ደረጃ የለም፡፡
እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። ሉቃስ 10፡29
10.    ክብሩ ይገባኛል ማለት
ትእቢተኛ ስው ስራውን ከመስራትና ውጤትን ከማምጣት በላይ በጣም የሚያሳስው መጨረሻ ላይ ክብሩ ለማን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ክብሩ ለእርሱ ካልሆነና እርሱ የማይጠራ ከሆነ ምንም ነገር ለማድረግ አይፈልግም፡፡ እርሱን በግል የማይጠቅመው ከሆነ ማንንም ሰው አውጥቶ ለመጣል ፈጣን ነው፡፡ እርሱ በግል የማይጠቀምበት ካልሆነ በቡድን ለሚገኘው ስኬት ግድ የለውም፡፡ እርሱን ብቻ የሚያስጠራው ፣ የሚያስከብረውና የሚጠቅመው ከሆነ ደግሞ ምንም ነገር ለማድረግ ይተጋል፡፡
ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ፊልጵስዩስ 2፡21
11.     ሁሉንም በራስ አቅዶ መስራት ነው፡፡
ትእቢተኛ ሰው ሁሉንም ነገር እራሱ በአእምሮው አቅዶ ነው የሚሰራው፡፡ ትእቢተኛ ሰው እግዚአብሄር ሃሳቡነ እንዲባርክለት እንጂ የእግዚአብሄርን ሃሳብ አይፈልግም፡፡ ትእቢተኛ ስው እግዚአብሄርን የሚፈልገው በጣም ለጥቂይት ነገር ብቻ ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ለራሱ በቂ ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው በራሱ ማስተዋል ይደገፋል፡፡ ትእቢተኛ ሰው ከልቡ ጌታ ቢፈቅድ የሚለው ነገር የለም፡፡ ትእቢተኛ ሰው ጌታ የምፈልገውን ነው የሚፈቅደው ብሎ ነው የሚታለለው፡፡
አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። ያዕቆብ 4፥13፣16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment