Popular Posts

Saturday, February 10, 2018

ስለ አንደበትዎ ማወቅ የሚገባዎ አምስት ነገሮች

ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። ያዕቆብ 3፡2-10
1.      አንደበት ከፍተኛ ተፅእኖ ያደርጋል፡፡
አንደበት በሚሰማው ላይ ከፍተኛ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅእኖ አለው፡፡ አንደበት ያለው እምቅ ጉልበት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ ምሳሌ 10፡11
2.     አንደበት ሊናቅ አይገባውም፡፡
አንደበት ትንሽ ክፍል ቢመስልም ነገር ግን ተፅእኖው እጅግ በጣም ታላቅ ነው፡፡ ትልቅን መርከብ አንድ ትንሽ መሪ እንደሚመራው ሁሉ የሰውን ህይወት የሚመራው አንድ ትንሽ የሰውነት ክፍል አንደበት ነው፡፡ አንድ ትንሽ እሳት ትልቅ ጫካን እንደምታቃጥል ሁሉ አንደበት ትንሽ ሆና ታላላቅ ነገሮችን ታበላሻለች፡፡
አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ። መዝሙር 141፡3
3.     አንደበት የስጋ ዋና ነው፡፡
የስጋ ምኞት ሃጢያተኛ ባህሪ በአንደበት ይገለፃል፡፡ የሰው የስጋ ምኞት ሁኔታ የሚታየው በአንደበት ነው፡፡ የስጋ ምኞት ዋናው አንደበት ነው፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን በመናገር ይረካል፡፡ ስጋ የሚመካው በመናገር በመናገር በመናገር ነው፡፡  ስጋ ንግግርን ሲከለከል ይጮሃል፡፡
እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። ማቴዎስ 12፡34
4.     አንደበትን ለመግራት ቀላል አይደለም፡፡
አንደበት ለመግራት ጥረትን ይጠይቃል፡፡ አንደበት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የሰውነት ክፍል ነው፡፡ አንደበት ከፍተኛ ክትትል ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ የምንናገረው ነገር ከመነገሩ በፊት በራሳችን መቀመስና መመርመር አለበት፡፡ በንግግር ዘና የምንልበት ነገር የለም፡፡ አንደበት አጥብቆ የሚጠብቀው ሰው ይፈልጋል፡፡
የሰው አንደበቱን የመጠበቅ አቅሙ ውስን ስለሆነ እራሱ ቀምሶ አጣጥሞ የሚያሳልፈው ጥቂት ቃል ካልሆነ በስተቀር ብዙ ቃል መናገር የለበትም፡፡
ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን? ኢዮብ 12፡11
በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። ምሳሌ 10፡19
5.     አንደበት ጥፋቱ ታላቅ ነው፡፡
አንደበት ሰውን ያነሳል ፡፡ አንደበት ሰውን ይጥላል፡፡ በአንደበት በአለም ችግር ላይ ችግር ልንጨምር እንችላለን፡፡ በአንደበት ለአለም ችግር መፍትሄ አንሰጣለን፡፡ በቃለዓችን ለሰዎች የእግዚአብሄርን ፀጋ እናካፍላለን፡፡ በእንደበታችን ሰዎችን እናፈርሳለን እናሰናክላለን፡፡  
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29
ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ 1ኛ የጴጥሮስ  3፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #አንደበት #ምላስ #አፍ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ፀጋ #እሳት #መልካምቀኖች #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment