Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, February 14, 2018

የፍቅር ምዕራፍ

ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4-7
ፍቅር ይታገሣል፥
ፍቅር አይቸኩልም ፣ ፍቅር አያስቸኩልም ፣ ፍቅር ይጠብቃል ፣ ፍቅር ጊዜ ይወስዳል ፣ ፍቅር የተረጋጋ ነው፡፡
ቸርነትንም ያደርጋል፤
ፍቅር ያካፍላል ፣ ፍቅር መልካምነትን ያደርጋል ፣ ፍቅር ሰዎች ሲጠቀሙ ይደሰታል ፣ ፍቅር ለሌሎች ሲያካፍል ደስ ይለዋል፡፡ ፍቅር የረካ ስለሆነ ሲሰጥ ይረካል፡፡
ፍቅር አይቀናም፤
ፍቅር ያረፈ ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር አይፎካከርም፡፡ ፍቅር ከክፉ የአለም ውድድር በገዛ ፈቃዱ ያቋረጠ ነው፡፡ ፍቅር በሌላው ማግኘትና መሳካት ደስ ይለዋል፡፡ ፍቅር በሰው ውስድቀት አይደሰትም፡፡ ፍቅር የሌላው ውድቀት እርሱን ከፍ እንደማያደርገው ያውቃል፡፡ ፍቅር ሌላው ያገኘው በእርሱ ማጣት እንደሆነ አያስብም፡፡ ፍቅር በረከቱን ሊወስድበት የሚችል ማንም እንደሌለ ያውቃል፡፡ ፍቅር አይቀናም፡፡ ፍቅር በሌላው መሳካት ሰላሙን አያጣም፡፡ 
ፍቅር አይመካም፥
ፍቅር ትሁት ነው፡፡ ፍቅር አይመካም፡፡ ፍቅር አይዳፈርም፡፡ ፍቅር ያለው ሁሉ የተሰጠው እንጂ የራሱ እንዳይደለ ያስባል፡፡ ፍቅር እንዳይወድቅ ይፈራል እንጂ አይመካም፡፡ ፍቅር በማንነቱ ስለረካ ዝቅ ይላል፡፡ ፍቅር የእርሱ ዝቅ ማለት ምንም እንደማያጎድልበት ያውቃል፡፡ ፍቅር ባለበት ደስተኛ ነው፡፡ ፍቅር ያለ አቅሙ አይንጠራራም፡፡
አይታበይም፤
ፍቅር ሌላው ላይ ከፍ አይልም፡፡ ፍቅር ሌላው ላይ ለመታበይ ሌላውን አይጥልም፡፡ ፍቅር ቁጥብ ነው፡፡ ፍቅር የትእቢት ንግግርን አያወጣም፡፡ ፍቅር በራሱ አይደገፍም፡፡ ፍቅር በሌላው ላይ ከፍ በማለት አይረካም፡፡ ፍቅር የሌላው መነሳት እንጂ ውድቀት አያስደስተውም፡፡
የማይገባውን አያደርግም፥
ፍቅር ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል፡፡ ፍቅር በምንም ሁኔታ ትክክለኛውን ነገር ማድረጉን እርግጠኛ ይሆናል፡፡ ፍቅር በስርአት ይኖራል፡፡ ፍቅር ስርአትን እይጥስም፡፡ ፍቅር የመፍትሄ እንጂ የችግር መንስኤ ላለመሆን ይጠነቀቃል፡፡ ፍቅር ጨዋ ነው፡፡ ፍቅር ማንንም ላለመጉዳት በስርአት ይኖራል፡፡ ፍቅር ስርአት አልበኛ አይደለም፡፡  
የራሱንም አይፈልግም፥
ፍቅር በራሱ ጥቅም ላይ የሙጥኝ አይለም፡፡ ፍቅር የእኔ ካልሆነ ሁሉ ይቅር አይልም፡፡ ፍቅር ለኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን አይልም፡፡ ፍቅር የሌሎችንም ጥቅም ይጠብቃል፡፡ ፍቅር አብሮ እንጂ ብቻውን ማደግ አይፈልግም፡፡ ፍቅር ለሌላው ግድ ይለዋል፡፡ ፍቅር የራሱን ስሜት ብቻ አይሰማም፡፡
አይበሳጭም፥
ፍቅር ነገሮችን ይተዋል፡፡ ፍቅር ቶሎ ይቅር ይላል፡፡ ፍቅር ድንበሩን ያውቃል፡፡ ፍቅር የራሱን ስለማይፈልግ የሚያጣው ነገር የለም፡፡ ፍቅር በጉልበቱ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ፍቅር ለእግዚአብሔር መንገድን ይተዋል፡፡ ፍቅር በራሱ ነገሮችን ያላግባብ ለመቆጣጠር ስለማይፈልግ ተረጋገቶ ይኖራል፡፡ ፍቅር ለእግዚአብሔር ቁጣ ስፍራ ይሰጣል እንጂ ራሱ አይበቀልም፡፡ ፍቅር ሰላሙን ይጠብቃል፡፡
በደልን አይቆጥርም፤
ፍቅር በደልን ይረሳል፡፡ ፍቅር ይረዳል፡፡ ፍቅር ይሸከማል፡፡ ፍቅር ይተዋል፡፡ ፍቅር ነገሮችን ያልፋል፡፡ ፍቅር ከመበደሉ በላይ ለግንኙነቱ ዋጋ ይሰጣል፡፡ ፍቅር ሰው ሊበድል እንደሚችል ተዘጋጅቶ ይገባል፡፡ ፍቅር ለመበደል ስፍራ ይተዋል፡፡ ፍቅር እንዴት ተነካሁ አይልም፡፡ ፍቅር የማይነካ አይደለም፡፡ ፍቅር ከአዲስ ይጀምራል፡፡
ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤
ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል፡፡ ፍቅር ከአመፅ ጋር ላለመተባበር ይጠነቀቃል፡፡ ፍቅር ከአመፃ ይርቃል፡፡ ፍቅር በአመፃ የሚገኝን ጥቅም ይንቃል፡፡፡ ፍቅር በምንም በምንም ይገኝ ጥቅም ብቻ ላግኝ አይልም፡፡ ፍቅር የመርህ እርምጃን ይራመዳል፡፡ የሚጠቅምም ቢሆን ፍቅር የሚያደርጋቸውና የማያደርጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍቅር አመፃን ይፀየፋል፡፡ ፍቅር ከእውነት ጋር ይቆማል፡፡ ፍቅር ለእውነት ይሰራል፡፡
ሁሉን ይታገሣል፥
ፍቅር ሁሉን ይታገሳል፡፡ ፍቅር ልቡ ሰፊ ነው፡፡ ፍቅር ሁሉ ሰው እንደኔ ይሁን አይልም፡፡ ፍቅር ከእርሱ የተለዩ ሰዎች ስህተት አይመስሉትም፡፡ ፍቅር ከእርሱ ለተለዩ ሰዎች ቦታ አለው፡፡ ፍቅር እኔን ካልመሰላችሁ አይልም፡፡ ፍቅር ከማይመስሉት ጋር ራሱን ያስተባብራል፡፡ ፍቅር የማይመስሉትን ሰዎች አውጥቶ አይጥልም፡፡ ፍቅር ከእርሱ ከተለዩ ሰዎች ጋር አንድ የሚያደርገውን ነገር ፈልጎ በዚያ ያፀናል፡፡ ፍቅር ልዩነትን አያጋንንም፡፡ ፍቅር ለአንድነት ይተጋል፡፡
ሁሉን ያምናል፥
ፍቅር ሁሉም በፊቱ የከበረ ነው፡፡ ፍቅር የሚንቀው ሰው የለም፡፡ በፍቅር ፊት የማይጠቅም ሰው የለም፡፡ ፍቅር ሁሉንም ያምናል፡፡ ፍቅር ሁሉም ሰው ጥንካሬ እንዳለው ያውቃል፡፡ ፍቅር እያንዳንዱ ሰው ከእርሱ የሚሻልበት ነገር እንዳለ ያውቃል፡፡ 
ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥
ፍቅር ለሁሉም ተስፋ አለው፡፡ ፍቅር ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ፍቅር ለሁሉ ተስፋው ሙሉ ነው፡፡ ፍቅር ሊነሳ የማይችል ሰው እንዳለ አያምንም፡፡ ፍቅር ማንም ሰው ሊለወጥ እንደሚችል ያምናል፡፡
 በሁሉ ይጸናል።
ፍቅር ወረተኛ አይደለም፡፡ ፍቅር ስልቹ አይደለም፡፡ ፍቅር አዳዲስ ነገር ለመፈለግ አይንከራተትም፡፡ ፍቅር ይቆያል፡፡ ፍቅር ይጠብቃል፡፡ ፍቅር ይታገሳል፡፡ ፍቅር ይረካል፡፡ ፍቅር ብዙ ነገር አያምረውም፡፡ ፍቅር አይለቅም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ፍቅር #ምንጭ #መውደድ #ይታገሣል #ቸርነት #አይቀናም #አይመካም #አይታበይም #አይበሳጭም #በደል #ስሜት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ማስተዋል #ልብ #መሪ  

No comments:

Post a Comment