Popular Posts

Monday, February 12, 2018

ፍቅር የሚፈተነው

ሰው ሁሉ ፍቅር ያለው ይመስላዋል፡፡ በሰላም ጊዜ ፍቅር ይቀላል፡፡ ነገር ሲጠነክር ጥሎ የሚጠፋ ፍቅር ፍቅር አይደለም፡፡ ነገር ሳይመች የሚተው ፍቅር አይደለም፡፡ መንገድ ሲያስቸግር የሚለይ ፍቅር ሳይሆን ራስ ወዳድነትና ተራ ስሜት ነው፡፡   
በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ምሳሌ 24፡10
ፍቅር ግን በሁኔታዎች ውስጥ ይፈተናል፡፡ ፍቅር የሚፈተንባቸው ሶስት መንገዶች፡-
1.      ፍቅር የሚፈተነው ለመውደድ ምክኒያት ስናጣ ነው፡፡
ፍቅር የሚፈተነው የምንወደው ሰው ሲለወጥ ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው የምንወደው ሰው ሲጠላን ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው ምንም ያህል ብንወደው የምንወደው ሰው ሳይረዳ ሲቀር ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው እየወደድነው ምንም እንዳልተፈጠረ ሲሆን ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው ለፍቅራችን ምላሽ ስናጣ ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው ለፍቅራችን ምላሽ ጥላቻ እና መገፋት ሲሆን ነው፡፡ የዚያን ጊዜ የሚጠፋ ፍቅር ፍቅር ሳይሆን ተራ ስሜት ነው፡፡ የዛን ጊዜ የሚቀጥል ፍቅር ተፈትኖ የወጣ እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡ ሁኔታዎችን ሳያይ መልካምን በማድረግ የሚቀጥል ፍቅር እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡ ሰው ክፉ አለመለካከቱን ሲያሳየን መልካም አመለካከትን የምናሳይ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር አለን፡፡ በመልካም የምናሸንፍ እንጂ በክፉ የምንሸነፍ ካልሆነ ያ እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡
ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ሮሜ 12፡20-21
2.     ፍቅር የሚፈተነው ጊዜው እየሄደ ሲሄድ ነው
ስሜት ተለዋዋጭ ነው፡፡ ስሜት አይቆይም፡፡ ስሜት አይዘልቅም፡፡ ስሜት አይፀናም፡፡ ፍቅርንና ስሜትን ለመለየት ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ ፍቅር የምንለው ነገር በራሱ እየቀነሰ ከሄደ ፍቅር ሳይሆን ስሜት ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር እየጨመረ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ እውነት ነው ፍቅር ትጋትን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ስራን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ማስተዋልና ጥበብን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር በየጊዜው መነቃቃትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁኔታ ከተሟላ ፍቅር እየጨመረ እየጨመረ ነው የሚሄደው እንጂ እውነተኛ ፍቅር እየቀነሰ አይሄድም፡፡  
ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል። መኃልየ መኃልይ 8፡7
3.     ፍቅር የሚፈተነው በችግር ጊዜ ነው፡፡
ፍቅር የሚፈተነው በዝቅታ ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው የምንወደው ሰው የምንወደው በአንድና በአንድ ምክኒያት ብቻ ሲሆን ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው የምንወደውን ሰው የምንወደው መውደድ ሃፊነታችን እንደሆነ ስንረዳ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው ከሌላው ወገን የምንጠቀመው ምንም ነገር ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው የምንወደው ሰው ሲደክም ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው በህይወቱ የምንወድለት ምክኒያት ሲጠፋ ነው፡፡ ፍቅር የሚፈተነው መግባባት ሲጠፋ ነው፡፡  
በፍቅረኞች ቀን አካባቢ ሰውን መውደድ ሊቀል ይችላል ነገር ግን ሰውን በዝቅተኛ የህይወቱ ደረጃ ላይ መውደድ ግን እውነተኛ ፍቅርን ይጠይቃል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ሌላውን በመረዳት መሸከም ይጠይቃል፡፡  
ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 1ኛ ዮሐንስ 4፡10
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መውደድ #ስሜት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ማስተዋል #ልብ #መሪ  

No comments:

Post a Comment