Popular Posts

Follow by Email

Sunday, February 25, 2018

የትእቢት ምንጭ

ትእቢት በእግዚአብሄር ፊት እጅግ አፀያፊ ነገር ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ትእቢተኛ ለሁን ብሎ ላይሆን ይችላል ትእቢተኛ የሚሆነው፡፡ ትእቢት ቀስ በቀስ ሰው ላይ የሚያደባና ሰውን የሚጥል የሃጢያት ማታለል ነው፡፡ ነገር ግን ትእቢት የሚመጣበትን ምንጩን ማወቅ ከትእቢት የምንጠበቅበትን መንገድ ይመራናል፡፡  
እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል። መዝሙር 138፡6
ትእቢት ካለማወቅ ይመጣል
እግዚአብሄርን የሚያውቁ ሰዎች ትሁታን እንጂ ትእቢተኛ አይሆኑም፡፡ ትእቢት እግዚአብሄርን በሚገባ ካለማወቅ ይመጣል፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅንና በተረዳን መጠን መንፈሳችን እየተሰበረ ትሁት እየሆንን ራሳችንን እያዋረድን እንጂ ትእቢተኛ እየሆንን አንመጣም፡፡ ጥቂት እውቀት ታስታብያለች፡፡ ትእቢት የሚያመለክተው የእግዚአብሄርን ሃይል በሚገባ አለማወቅን ነው፡፡ ሰው በትእቢት የሚስተው ቅዱሳን መፅሃፍትንና የእግዚአብሄርን ሃይል በሚገባ ካለመረዳት ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ። ማቴዎስ 22፡29
ትእቢት ከስጋት ይመጣል
በህይወቱ በጌታ ያልታመነ ሰው በእግዚአብሄር አቅርቦት ያልተማመነ ሰው ስጋቱ የሚገለፀው በትእቢት ነው፡፡ ትእቢት የእምነት ተቃራኒ ነው፡፡ ትእቢት የስጋት ምልክት ነው፡፡ በህይወቱ የተማመነ ሰው በህይወቱ የረካ ሰው ራሱ ከፍ ማድረግ ትእቢተኛ መሆን አያስፈልገውም፡፡ በራሱ ማንነት የተማመነ ሰው ትልቅነቱ ለማሳየት ምንም ማድረግ አያስፈልገውም፡፡ በራሱ የተማመነ ሰው ተፅእኖውን  ለክፉ ላለመጠቀም ይጠነቀቃል፡፡ ሃይል እንዳለው የሚያውቅ ሰው ጉልበቱን በመልካም ነገር ላይ ብቻ ለማዋል ያስባል፡፡ ሃይል እንዳለው በእርግጥ የማይተማመን ሰው ግን በክፉ ነገር ሁሉ ሃይሉን ይሞክራል፡፡ ትእቢት በልብ ያለን አለመረጋገትና ትእቢት ያሳያል፡፡
እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2፡4
ትእቢት ከራስ ወዳድነት ይመጣል
ትእቢት ከራስ ወዳድነት ይመጣል፡፡ በቂ ነገር እንዳለው የረካ ሰው በትህትና ሌሎችን ሊያገለግል ይተጋል፡፡ የረካ ሰው ሌላውን ሊያረካ ይተጋል፡፡ የተቀበለ ሰው ሊሰጥ ይተጋል፡፡ በልቶ ያልጠገነበ ሰው ግን ራስ ወዳድ ይሆናል፡፡ ራስ ወዳድ ደግሞ ሃሳቡን ሊያስፈፅም የሚችለው በከፍተኝነት ስሜት ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ከፍ ብሎ ካልታየ በስተቀር ወደኋላ የሚቀር ፍላጎቱ የማይሞላ ይመስለዋል፡፡
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1
ትእቢት ከዝቅተኝነት ስሜት ይመነጫል
የበላይ ሰወ የበላይ ለመምሰል አይጥርም የበላይ ነውና፡፡ የበታች የሆነ ሰው ግን የበላይ ለመምሰል ይጥራል የበታች ነውና፡፡ እንዲሁ የዝቅተኝነት ስሜት ያለበት ሰው የዝቅተኝነት ስሜቱን ለማካካስ የከፍተኝነትን ስሜት በማሳየት ትእቢተኛ ይሆናል፡፡ የዝቅተኝነት ስሜት የሌለበት ሰው ግን የሚያካክሰው ምንም የዝቅተኝነት ስሜት ችግር ስለሌለበትና በራሱ የረካ ስለሆነ ትእቢተኛ ሲሆን እንመለከትም፡፡ ራሱን የሚያውቅና የዝቅተኝነት ስሜት የሌለበት ሰው ትሁት ለመሆን አይቸገርም፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-5
ትእቢት ከእረፍት ማጣት ይመጣል
ሰው በጌታ እንዲያርፍና እንዲተማመን ተፈጥሮአል፡፡ ሰው የሚያርፍበትና የሚተማመንበት አንድ ነገር ይፈልጋል፡፡ ሰው በጌታ ካላረፈ የሚያርፈበት ሌላ ነገር ይፈልጋል፡፡ በጌታ ደስ ያለው ሰው ትሁት እንጂ ትእቢተኛ አይሆንም፡፡ በጌታ ያረፈ ሰው የሚያርፍበት ነገር ስላገኘ ከእረፍት ተነስቶ ሌሎችን ያገለግላል፡፡ በጌታ ያላረፈ ሰው ግን በራሱ ጉልበትና እውቀት ለማረፍ ሲሞክር ትእቢተኛ ይሆናል፡፡ በጌታ ያረፈ ሰው በራሱ ማረፍ አይጠበቅበትም፡፡ በጌታ የተማመነ ሰው በራሱ መተማመን አይጠበቅብትም፡፡ በጌታ ያልተማመነ ሰው ግን ተጣልቶም ተዋግቶም በክንዱ ነገሮችን ማድረግ እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡  
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ያዕቆብ 3፡14
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ያዕቆብ 4፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment