ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ። ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ። መዝሙር 50፡7-14፣23
የእስራኤል ህዝብ መሥዋዕት የማቅረብ ትርጉሙን አልተረዳውም ነበር፡፡ የእስራኤል ህዝብ መሥዋዕት የሚሰዋው እንደ ልምድ ነበር፡፡ የእስራኤል ህዝብ መሥዋዕት የሚሰዋው ግዴታው ስለነበረ ይመስላል፡፡
ለእግዚአብሄር ግን መሥዋዕት የበግና የፍየል ጉዳይ አይደለም፡፡ መሥዋዕት ማድረግ ማለት የከብት ሃብታችሁን ለእግዚአብሄር ማካፈል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሃብታችሁን አይካፈልም፡፡ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእግዚአብሄር ነው፡፡ ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሄር ናት፡፡
ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት: ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ መዝሙር 24፡4.
መስዋእት ማድረግ ማለት እግዚአብሄር ተርቦ ለእግዚአብሄር በግ አርዶ ማብላት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር መስዋእት እንዲያደርጉ ያዘዘው ርቦትና ጠምቶት አይደለም፡፡ ስጋ የምበላ ደም የምጠጣ ከሆነ ቢርበኝ ለአንተም አልነግርህም ይላል እግዚአብሄር፡፡
ታዲያ እግዚአብሄር ምን ፈልጎ ነው መስዋእት አድርጉ ያለው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡
እግዚአብሄር የፈለገው ምስጋናን ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈለገው በበጉና በፍየሉ ላይ ተጭኖ የሚመጣውን ምስጋና ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈለገው በጉንና ፍየሉን የሚያመጣውን ሰው የልብ ምስጋናን ማየት ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈለገው የመስዋእት አድራጊውን የልብ ምስጋና ነው፡፡
በጉበና ፍየሉ ምስጋናውን የሚሸከም ተሸካሚ እንጂ ስጦታ አይደለም፡፡ በጉና ፍየሉ የልብን ምስጋና የሚያሳይ መጠቅያ እቃ እንጂ ራሱ ስጦታ አይደለም፡፡ በጉና ፍየሉ ምስጋናውን ማሳያ መንገድ እንጂ በራሱ ምስጋና አይደለም፡፡
የእስራኤል ህዝብ መስዋእት ሊያደርጉ ሲሄዱ በመጀመሪያ ደረጃ በእግዚአብሄር ፊት ሊታዩ ነው የሚሄዱት፡፡ እግዚአብሄር የሰውን የህይወት ጤንነት የሚያየው በምስጋናው ነው፡፡
በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። ዘጸአት 34፡23
ሰው ወደእግዚአብሄር ሲገባ ፕሮቶኮሉ ወይም ስርአቱ በምስጋና መሆን አለበት፡፡
ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤ መዝሙር 100፡4
እግዚአብሄር መስዋእትን ሲቀበል መጀመሪያ የሚያየው መስዋእት አድራጊውን ነው፡፡
አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ዘፍጥረት 4፡4
አሁንም እግዚአብሄርን በምናገለግላቸው መንገዶች ሁሉ አገልግሎታችንን ከማየቱ ጌታ ልባችንን ያያል፡፡ በልባችን ምስጋና ከሌለ የምናገለግለው ከምስጋና ተነስተን ካልሆነ ባዶ ሃይማኖታዊ ወግ እየፈፀምን እንጂ ጌታን እያገለገልን አይደለም፡፡
ስናገለግል ፣ ስንሰጥ ፣ ህብረት ስናደርግና ስንመሰክር ከምስጋና ልብ ማገልገል አለብን፡፡
ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ። መዝሙር 50፡14፣23
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ምስጋና #መዳን #እምነት #መሥዋዕት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment