Popular Posts

Monday, August 20, 2018

የማርያም ምሳሌነት

ለሃጢያታችን ለመስቀልና ለመሞት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ መድር የመጣው በማርያም አማካኝነት ነው፡፡ ማርያም የኢየሱስ እናት ለመሆን በእግዚአብሄር የተመረጠች ሴት ነች፡፡
መልእክቱን ለእለት ተእለት ህይወታችን ትምህርትን መውሰድ እንጂ መፅሃፍ ቅዱስን ስናነብ እንደ ታሪክ ብቻ ማንበብ የለብንም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስን ስናነብ በመፅሃፍ ቅዱስ ታሪካቸው የተፃፈ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት እንደተራመዱ መረዳት ለአሁኑ ህይወታችን ምሳሌ ይሆነናል፡፡
ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡11
በመፅሃፍ ቅዱስ የማርያምን ታሪክ ስናነብ ከማርያም ህይወትና መልካም ባህሪ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ማርያም የእምነት ሰው ነበረች
ማርያም ወንድ ሳታውቅ ልጅ ትወልጃለሽ ስትባል በእምነት አሜን ይሁንልኝ አለች፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል እንዳለ መቀበል እምነት ይጠይቃል፡፡ ይህ የእግዚአብሄርን ቃል እንደሚሰራ እንደ አምላክ ቃል መቀበልን ይጠይቃል፡፡  እግዚአብሄር ካለ የማይቻል ነገር ይቻላል ብላ ማርያም አመነች፡፡ ማርያም ሳታይ በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል አመነች፡፡
ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። የማቴዎስ ወንጌል 1፡16፣18
ማርያም የእግዚአብሄር ፈቃድ የምትፈልግ ሴት ነበረች
ማርያም ኢየሱስን እንደምትወልድ መላኩ ሲያበስራት ያለችው አንድ ነገር እንደቃልህ ይሁንልኝ ነው፡፡ ማርያም የራስዋን ነገር የማትፈልግ የእግዚአብሄርን ነገር የምታስቀድም ሴት ነበረች፡፡ ማርያም እግዚአብሄር ከፈለገው ይሁን እግዚአብሄር ካልፈለገ ይቅር የምትል የእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ በህይወትዋ እንዲሆን የምትፈልግ ሴት ነበረች፡፡
ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። የሉቃስ ወንጌል 138
ማርያም ትሁት ነበረች
ማርያም ትሁት ሴት ነበረች፡፡ ማርያም በእግዚአብሄር ፊት ራስዋን የምታዋርድ ሴት ነበረች፡፡ ማርያም ነውርን የምትንቅ ሴት ነበረች፡፡ ናቀችው፡፡ ሰዎች በሰዎች እንዳይነቀፉና ነውረኛ እንዳይባሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከማድርግ ይመለሳሉ፡፡ ማርያም ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድርግ ከጋብቻ በፊት የማርገዝን ነውርን ናቀች፡፡
ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም፦ እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። የሉቃስ ወንጌል 2፡34-35
ሰው የወለደው ልጁ እንደ ወንጀለኛ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ማየት ያማል፡፡ ማርያም ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመታዘዝ ያንን ህመም ዋጥ አደረገች፡፡ ማርያም የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም ሰዎች ነውር ነው ከሚሉት ነገር ይልቅ የእግዚአብሄርን ጎሽታ መረጠች፡፡  ማርያም ከሰው ከሚገኘው ክብር ይልቅ ከእግዚአብሄር የሚገኘውን ክብር መረጠች፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ወደ ዕብራውያን 12፡1-2
ማርያም ትዕግሥተኛ ነበረች
ማርያም እግዚአብሄር በመላኩ ከተናገራት በኋላ እግዚአብሄር የተናገረው እስኪፈፀም በዝምታ ታግሳ ጠበቀች፡፡
ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። የሉቃስ ወንጌል 2፡19
ማርያም ራስዋን በእግዚአብሄር ፊት የምታዋርድ ነበረች
ማርያም እግዚአብሄር በእርስዋ ያደረገው ነገር ሁሉ እንደሚገባት አልቆጠረችውም፡፡
ማርያምም እንዲህ አለች፦ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። የሉቃስ ወንጌል 1፡46-48
ማርያም እግዚአብሄርን በነገር ሁሉ የምታመሰግን ሴት ነበረች
ማርያምም እንዲህ አለች፦ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የሉቃስ ወንጌል 1፡46-49
ማርያም እግዚአብሄርን የምትወድ እንደ አምላክነቱ እውቅና የምትሰጥ እግዚአብሄርን የምታመልክ ሴት ነበረች፡፡
ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። የሉቃስ ወንጌል 1፡49
ማርያም በኢየሱስ የምታምን ሌሎችም እንዲከተሉትና እንዲታዘዙት የምትናገር ነበረች
እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ (ኢየሱስ) የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። የዮሐንስ ወንጌል 2፡5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ድንግል #ፀሎት #ልመና #ብፅዕት #ማሪያም #ትህትና #ምስጋና #አምልኮ #ትእግስት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #ምስጋና

No comments:

Post a Comment