Popular Posts

Tuesday, April 3, 2018

ስንሞት ምን እንሆናለን ?

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡የሰው መኖሪያ ቤቱ እና ስጋው ከምድር አፈር ቢበጅም ሰው ግን አፈር አይደለም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ በስጋ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 2፡7
እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ስጋውን ከምድር አፈር አበጀው፡፡ የሰው ስጋ ከምድር አፈር ስለተበጀ የህይወት እስትንፋስ እፍ እስኪባልበት ጊዜ ድረስ ስጋው ሙት ነበር፡፡ እግዚአብሄር የህይወት እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት የሰው ስጋ ስሜት ያለው ፣ ፈቃድ ያለውና ሃሳብ ያለው አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር በሰው ስጋ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት የሰው ስጋ ግኡዝ አካል ነበር፡፡ እግዚአብሄር በሰው ስጋ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት ሰው ህያው ነፍስ ያለው አልነበረም፡፡
እግዚአብሄር በፈጠረው የሰው አካል አፍንጫ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ካለበት በኋላ ሰው ህያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡
ሰው ሲሞት አይጠፋም፡፡ ሰው ሲሞት አይበንም፡፡ ሰው ሲሞት መንፈሱ ከስጋ ይለያል፡፡ የማንኛውም ሰው በስጋ መሞት ከስጋ መለየት ነው፡፡ የውስጠኛው ሰው መንፈስ ከስጋ ተለይቶ ወደ መንፈሳዊው አለም ይሄዳል፡፡ የውጭው ሰው ስጋው ከመንፈስ ተለይቶ ወደ መቃብር ይገባል፡፡
ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ሉቃስ 16፡22
ሰው ወዲህና ወዲያ ለመሄድ ፈቃድ ያለው በምድር ላይ ብቻ ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ሲኖር ብቻ ነው የፈለገበት የሚሄደው ያልገፈልገበት የማይሄደው ፡፡ ሰው በስጋ ሲሞት መንፈሱ ከስጋው ሲለይ ግን በመላእክት ይወሰዳል እንጂ ራሱን የትም አይወስድም፡፡ ሰው በስጋ ሲሞት ራሱ ወደፈለገበት ቦታ አይሄድም፡፡    
ሰው የተገኘው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ሲሞት መኖሪያ ስጋው ወደ ነበረበት ምድር ይመለሳል፡፡ ሰው ግን ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሄር ይመለሳል፡፡
አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። መክብብ 127
ሰው ሲሞት ከስጋ ስለሚለይ በስጋ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሰው መንቀሳቀስ ስለማይችእል መላእክት ይወስዱታል፡፡
ለሰው አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም ፍርድ ይጠብቀዋል፡፡ ሰው የኢየሱስን አዳኝነት የሚቀበለው በስጋ ውስጥ እያለ ነው፡፡ ሰው ከስጋ ከተለየ መላእከት ወደሚወስዱት ቦታ ይሄዳል እንጂ ጌታን ለመከተል ወይም ላለመከተል መወሰን አይችልም፡፡  
ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እብራዊያን 9፡27
በምድር ላይ ጌታ ኢየሱስን አንደ አዳኙ የተቀበለ ሰው ሁሉ ወደዘላለም እረፍት ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ሃጢያት በመስቀል ላይ እንደዲሞት የሰጠውን ኢየሱስን በምድር ላይ ያልተቀበለ ሰው ለዘላም ከእግዚአብሄር ይለያያል፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #አፈር #ስጋ #ቤት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ

No comments:

Post a Comment