Popular Posts

Thursday, March 22, 2018

ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን?

በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን? ምሳሌ 24፡10-12
በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ የተባለለት ኢዮብ ድምፅ ለሌለው ድምፅ በመሆን ፣ ተሰሚነቱን ተጠቅሞ ለተገፋው በመቆምና ለተጨቆነው ሲከራከር ታላቅ የሆነበትን ምክኒያቶች ልናይ እንችላለን፡፡
ለድሀው አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ። ኢዮብ 29፡6
የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና። ኢዮብ 29፡12
ተሰሚነት ሌሎችን የመጥቀም እድል ነው፡፡ ተወዳጅነት ሌሎችን የማገልገል ሃላፊነት ነው፡፡ ዝነኝነት ተሰሚነታችንን ተጠቅመን ሌሎችን የመጥቀም ስልጣን ነው፡፡ እግዚአብሄር ተሰሚነትን የሚሰጠን ካለ ምክኒያት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ተሰሚነትን የሚሰጠን የልቡን ሃሳብ እንድናስፈፅም ነው፡፡
ስለዚህ ነው ካለ ፍርድ ወደ ሞት የሚነዱትን እንድንታደግ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሊታረዱ የተወሰኑትን ለማዳን ድምፃችንን እንድናሰማ የሚጠብቅብን፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ተሰሚነታችንን ተጠቅመን ለራ መከራከል ለማይችለው እንድንከራከር የሚያስተምረን፡፡
መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። ኢሳያስ 1፡17
የፍርድ መጉደልን ካየህ የመናገር ሃላፊነት አለብህ፡፡ አላየሁም ማለት አትችልም፡፡ አላየሁም ብለህ ራስህን ብታታልል ትችል ይሆናል፡፡ አላየሁም ብለህ በሰው ገፊ ብትናገር ሰውን ማታለል ትችል ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ግን አላየሁን አልሰማሁም ማለት አትችልም፡፡ ሰውን ፈርተህ ከሆነ እርሱን ይበልጥ ስላልፈራህ እግዚአብሄር ያዝናል፡፡
ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። ምሳሌ 29፡25
እንዲውም እውነተኛ ሰውነትህ የሚታየው በሰላም እና በፍትህ ቀን አይደለም፡፡ እውነተኛ ሰውነትህ የሚታየው ንፁህ ሰው ሲገፋ ፣ ደካማ ሰው ሲጨቆንና ፍትህ ሲዛባ ስታይ ነው፡፡ የዛን ጊዜ ለደካማው ከቆምክ ጉልበት አለህ ማለት ነው፡፡ ለደካማው ካልቆምክ ይመስልሃል እንጂ ጉልበት የለህም ማለት ነው፡፡  
ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን? ምሳሌ 24፡10-12
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #መበለት #ድሃአደግ #ድሃ #ጭቆና #ፍትህ #ፍርድ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

No comments:

Post a Comment