Popular Posts

Saturday, March 3, 2018

ዘመኑን በትክክል መተርጎም

እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? ሉቃስ 12፡56
ዘመኑን በትክክል መተርጎም በዘመኑ የትኛውን ነገር ማድረግ የትኛውን ደግሞ አለማድርግ እንዳለብን እውቀት ይሰጠናል፡፡ ዘመኑን በትክክል መተርጎም ምንም ነገር ካለ ጊዜው እንዳናደርግ ይረዳናል፡፡ ዘመኑን በትክክል መተርጎም ጉልበታችንን አላስፈላጊ ነገር ላይ እንዳናባክን ይረዳናል፡፡ ዘመኑን በትክክል መተርጎም ብዙ ዘርተን ትንሽ እንዳናጭድ ይጠብቀናል፡፡ ዘመኑን በትክክል መተርጎም በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛውን ነገር በማድረግ ፍሬያማ እንድንሆን ያስችለናል፡፡
እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች ዐለቆች ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፡፡” 1ኛ ዜና. 12÷32
ዘመኑን በሚገባ አለመተርጎም በዘመኑ የተከፈተልንን ታላቅ እድል እንዳንጠቀም ያደርጋል፡፡ ሰላም በጣው ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ዘመኑን በትክክል አለመተርጎም ለሰላማችን የሚሆነውን ነገር ትተን በተራ ነገር ላይ ባተሌ በመሆን ህይወታችንን በከንቱ እንድናባክን ያደርገናል፡፡  
ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ሉቃስ 19፡41
በተከፈተልን እድል ለመጠቀም ጥበበኛ መሆን አለብን፡፡ ሞኝ ሰው የተከፈተለትን እድል ያባክነዋል፡፡ ሞኝ ሰው ቆይቶ ቢነቃ እንኳን ተመልሶ እድሉን አያገኘውም፡፡
ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። እብራዊያን 12፡17
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ኤፌሶን 5፡15-17
የእግዚአብሄርን ትክክለኛ ጊዜ የምንለየው እግዚአብሄን ስንፈልግ ስንፀልይ ከእግዚአብሄር ጋር ስንነጋገር ብቻ ነው፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ በልጅህ በኢየሱስ የመስቀል ስራ ልጅህ አድርገህ በቤተሰብህ ውስጥ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አንተን እፈልግሃለሁ፡፡ አንተ በህይወቴ እንድሆን የምትፈልገውን እንድሆን ፣ እንዳገኝ የምትፈልገውን እንዳገኝና እንዳደርግ የምትፈልገውን እንዳደርግ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ መሄድ ሲገባኝ አንድሄድ ፣ መቆም ሲገባኝ እንድቆም መጮህ ሲገባኝ እንድጮህና ዝም ማለት ሲገባኝ ዝም ማለት እንድችል የአንተን የጊዜውን አሰራር እረዳ ዘንድ ራሴን ላንተ እሰጣለሁ፡፡  እየመራኸኝ ስለሆነ አመሰግንሃለሁ፡፡ አንተ የሰጠኸኝን እድል አጥቼው ስለማልፀፀት አመሰግንሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፡፡  አሜን
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ዘመን #እድል #ዋጁ #ጥበብ #መተርጎም #ይሳኮር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment