Popular Posts

Follow by Email

Monday, March 5, 2018

ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጲያ ነቢያት

ኢየሱስ ለቤተክርስያን ከሰጣቸው የአገልግሎት ስጦታዎች አንዱ የነቢይነት አገልግሎት እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ይህ የነቢይነት አገልግሎት ቤተክርስትያን ፍፁንም አስከምትሆን ድስ የሚቀጥል አገልግሎት ነው፡፡
በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የነቢያት አገልግሎት በኢትዮጲያ በሃይል መነሳቱን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ደግሞ እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡ ይህ የነቢይነት አገልግሎት ደግሞ ካለነቀፋ አይደለም፡፡ የነቢይ አገልግሎት ነቀፋ አለበት ማለት ደግሞ የነቢያት አገልግሎት የለም ነቢያት የሉም ማለት በፍጹም አይደለም፡፡
በታማኝነትና በትጋት የእግዚአብሄርን ህዝብ የሚያገልግሉትን ነቢያት እግዚአብሄር ይባርካቸዋል፡፡ እኛም በዚህ አጋጣሚ እናመሰግናለን በአገልግሎታችሁ ተጠቅመናል እግዚአብሄር ይባርካችሁ ልንል እንወዳለን፡፡  
ነቢያት በቤተክትስትያን ውስጥ አሉ፡፡ ነቢያት በአሁን ዘመን ይሁን በሚመጣው ዘመን ይነሳሉ፡፡
በተለይ የኢትዮጲያን የነቢያት አገልግሎት የሚመለከት በአጠቃላይ ደግሞ ለአገልጋዮች መልእክት ማስተላለፍ ልቤ ወደደ፡፡
1.      ነቢያት ሆይ የእግዚአብሄርን ህዝብ ወደ ቃሉ መልሱ
የእግዚአብሄር ህዝብ ተጨንቆና ተጠቦ ወደ እናንተ ሲመጣ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ወደሚችል ወደ እግዚአብሄ ቃል መልሱት እንጂ ህዝቡን የእናንት ጥገኛ አታድርጉት፡፡ ህዝቡን ከእኔ አካባቢ አትራቅ እንጂ ትባረካለህ አትበሉት፡፡ ወደ እናንተ ሲመጣ ወደ እግዚአብሄር ቃል መለሱት ከእግዚአብሄር ቃል ጋር በማገናኘት በራሱ እንዲቆም እርዱት፡፡ ሰው ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው የእግዚአብሄርን ቃል ሰምቶ ሲያምን ነው፡፡ በእውነት ነፃ የሚያወጣው የእግዚአብሄርን ቃል ሰምቶ መታዘዝ ነው፡፡ ህዝቡ የእግዚአብሄርን ቃል ሰምቶ ሲታዘዝ ፍሬ ያፈራል፡፡
ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሃንስ 8፡32
2.     ነቢያት ሆይ የእግዚአብሄርን ክብር አትውሰዱ
የእግዚአብሄር ህዝብ የከበረ ህዝብ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ እግዚአብሄር አምላኩ የሆነለት ህዝብ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ እየተነሳ ያለ ህዝብ ነው፡፡
የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። ምሳሌ 4፡18
የእግዚአብሄር ህዝብ በክርስቶስ ደም የተገዛ ህዝብ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ የተባረከ ህዝብ ነው፡፡ አንድ ቀን ስላገለገላችሁት ለአመታት ሲያገለግሉት የቆዩትን የሌሎችን አገልጋዮች ሁሉ ምስጋና አትውሰዱ፡፡ አንዴ ስላገለገላችሁት በዘመኑ ሁሉ ሲረዳው የነበረውን የእግዚአብሄርን ክብር ጠቅልላችሁ አትውሰዱ፡፡
እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። ሉቃስ 17፡10
3.     ነቢያት ሆይ ነውረኛን ረብ አትፈልጉ
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
አገልግሎት ህዝብን መጥቀሚያ እድል እንጂ ከህዝብ መጠቀሚያ አይደለም፡፡ ስለምትብሉትና ስለምትጠጡት እግዚአብሄርን እመኑ፡፡ የእናንተን ምንጭ እግዚአብሄርን አድርጉ እንጂ ህዝቡን አታድርጉ፡፡ የእናንተን ምንጭ እግዚአብሄር ካደረጋችሁ በንፁህ ልብ ህዝቡን ማገልገል ትችላላችሁ፡፡  
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡2
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
4.     ነቢያት ሆይ ከተፃፈው አትለፉ
እግዚአብሄር ተሰሚነትን በሰጣችሁ መጠን ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ ምንም ያህል አዲስና አስደናቂ ነገር ለማምጣት ብትፈተኑም ከተፃፈው አትለፉ፡፡ ለአስተምሮታችሁም ይሁን ለልምምዳችሁ የተፃፈው ይበቃል፡፡ የተፃፈውን ለማጠናከር አትሞክሩ በራሱ ጠንካራ ነው፡፡ የመጨረሻ ስልጣናችሁ መፅሃፍ ቅዱስ ይሁን፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ያላለውን ለማለት መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ያልተደረገውን ለመለማመድ ፍሩ፡፡ ሃዋሪያው ጳውሎስ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከተፃፈው ላለማለፍ ራሱን ያዋርድ ነበር፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡6
5.     ነቢያት ሆይ ህዝቡ በራሳቸው እንዲቆሙ እርዱ
የእግዚአብሄር ልጅ የሆነ ሰው ሁሉ አግዚአብሄርን መስማት ይችላል፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ በዘለቄታነት የሚጠቅመው ችግር ሲገጥመው ነቢያትን መፈለግ ሳይሆን የእግዚአብሄርን መንፈስ መስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ ወደ እናንት ሲመጣ ራሱ እንዴት የእግዚአብሄርን ድምፅ መስማት እንደሚችል አስተምሩት፡፡ አሳን ከምትሰጠው አሳን ማጥመድ አስተምረው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ሮሜ 8፡14
6.     ነቢያት ሆይ ሌሎችን የአገልግሎት ስጦታዎች አታጣጥሉ፡፡  
የነቢይነትን አገልግሎት የሰጠው አንዱ ጌታ የወንጌላዊነትን አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ የመጋቢነትን አገልግሎት የሰጠ ጌታ የአስተማሪነትን አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ሁሉም አገልግሎቶች ለቤተክርስትያን ያስፈልጋሉ፡፡ ካለ ሁሉም አገልግሎቶች ቤተክርስትያን ሙሉ አትሆንም፡፡ ስለዚህ ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር አብራችሁ አገልግሉ፡፡ ሌሎችን አገልግሎቶች አታጣጠሉ፡፡
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡11-13
7.     ነቢያት ሆይ የሽማግሌዎችን ትእዛዝ አክብሩ
የቀደሙትን ሽማግሌዎችን አክብሩ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የሚነሳው በቀደመው ትውልድ ነው፡፡ ሽማግሌዎችን ስሙ አክብሩ፡፡ ሽማግሌዎችን ታዘዙ፡፡ እኛ የማናየውን ነገር ያያሉ ብላችሁ ለሽማግሌዎች ልባችሁን ክፈቱ፡፡ ለመታረም ራሳችሁን ትሁት አድርጉ፡፡ ስትታረሙ እንደተጣላቹ እንደተገፋችሁ አድርጋችሁ አትቆጡ፡፡ ሽማግሌን መስማት እግዚአብሄርን መስማት ሊሆን እንደሚችል አስታውሱ፡፡
ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡29
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5-6
8.     ነቢያት ሆይ ከማንም ጋር አትፎካከሩ
እግዚአብሄር በሰጣችሁ አገልግሎት ላይ ብቻ አተኩሩ ፡፡ እንደ እናንተ የተጠራ እናንተን ፍፁም የሚመስል ምንም አገልጋይ የለምና ከማንም ጋር አትፎካከሩ፡፡ የማንም ውድቀት የእናንተን መነሳት አያሳይም፡፡ ለአንድ መንግስት አብራችሁ እንደምትሰሩ መጠን የሌላው ውድቀት ግን የእናንተ ውድቀት አካል ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሰጣችሁ አገልግሎት ጋር ብቻ ተሽቀዳደሙ፡፡ እግዚአብሄር የሰጣችሁን አገልግሎት ለመጨረስ ሩጡ፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
9.     ነቢያት ሆይ ነቢይ ስለሆናችሁ ብቻ ቤተክርስትያን አትጀምሩ
ነቢይ ናችሁ ማለት በቤተክርስትያን ከሌሎች ጋር እንድታገለግሉ እግዚአብሄር አገልግሎት ሰጣችሁ እንጂ ቤተክርስትያን እንድትጀምሩ ስልጣን አይሰጣችሁም፡፡ እግዚአብሄር የሰጣችሁን የነቢይነት አገልግሎት ተሰሚነት ቤተክርስትያን ለመጀመር አትጠቀሙበት፡፡ እግዚአብሄር የሰጣችሁን ተሰሚነት የእግዚአብሄርን ህዝብ አንድ ለማድረግ የእግዚአብሄርን ህዝብ ለማገልገልና ለመጥቀም ተጠቀሙበት፡፡
10.    ነቢያት ሆይ እግዚአብሄር ካልሰጣችሁ አትናገሩ
የእግዚአብሄርን ነገር ሁሌ የምታውቁ እንደሆናችሁ የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መንፈስ እንደፈቀደ ብቻ የእግዚአብሄርን ነገር እንደምትረዱ ደግሞ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ሲናገር ለመናገር እግዚአብሄር ያልሰጣችሁን  ላለመናገር ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እግዚአብሄር ያላለውን ከመናገር በሰው ፊት ብትናቁ ይሻላል፡፡
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ኤርሚያስ 23፡16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነቢያት #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment