Popular Posts

Wednesday, March 14, 2018

ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እግዚአብሔር ይባርክ

ሰሞኑን ወንጌላዊያን አቢያተ ክርስትያናት ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እንደማይወዱና እንደሚሳደቡ ተደርጎ ሲቀርብ በአንድ ውይይት ላይ ሰምቻለሁ፡፡
የኦርቶዶክስን ቤተክርስተያን በማንኛውም ሁኔታ ብንጠላ ጥፋቱ የእኛ እንጂ የእነርሱ አይደሉም፡፡ የኦርቶዶክስን ቤተክርስትያን ባንወድ የምንጎዳው እኛ እንጂ እነርሱ አይደሉም፡፡ ምክኒያቱም እግዚአብሄር ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ይወዳል፡፡ እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል፡፡
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡3-5
የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የአብዛኞቻችን መገኛ ምንጭ ነች፡፡ መጀመሪያ ስለ መፅሃፍ ቅዱስ የሰማነው ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትርያን ነበር፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ነች በብዙ ነገር ውስጥ አልፋ ክርስትናን በምድራችን ያቆየችው፡፡ አብዛኞቻችን በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ ነው ያደግነው፡፡ አብዛኞቻችን ያደግነው የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን የፀሎትና የፆም መርሃ ግብር ተካፍለን ፆመን ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ግን የሃይማኖቱን ወግና ስርአት እንፈፅማለን እንጂ ህይወታችን ያልተለወጠ የስም ክርስትያኖች ብቻ ነበርን፡፡
እኔ በግሌ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያነ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ክትስትናን እንደሃይማኖት እንጂ ህይወቴ የተለወጠ አልነበረም፡፡ የወንጌላዊያን አብያተክርስተያናት አማኞች ስለኢየሱስ አዳኝነት ስለሃጢያቴ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ እንደሞተ ኢየሱስን እንደ አዳኝ አድርጌ ብቀበል እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ እንደሚቀበለኝና የዘላለም ህይወት እንደሚኖረኝ የነገሩኝን ቃሉን ሳምን ዳግመኛ ተወለድኩ፡፡ የዚያን ጊዜ ነው ስለጌታ ይበልጥ ለመማር የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ትቼ ወደ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስትያናት የተቀላቀልኩት፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ እንደእኔ መኝሃፍ ቅዱስን ከሚያምኑ ቅዱሳን ጋር ጌታን አመልካለሁ አገልግላለሁ፡፡
በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡22
በጊዜው የእግዚአብሄርን ቃል በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ለመማርና ለመለወጥ ከወንጌላዊያን አብንያተ ክትርስትያናት ጋር ተቀላቀልኩ እንጂ ዳግመኛ ለመወለድ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስትያናት አባል መሆን አያስፈልገኝም፡፡ ያዳነኝ ክርስቶስን እንደአዳኝ መቀበሌ አንጂ ያለሁበት ቤተክርስትያን አባልነት አይደለም፡፡ ዳግመኛ ሳልወለድ ኢየሱስን ሳልከተል በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ አባልነቴ ብቻ እንዳላዳነኝ ሁሉ የወንጌላዊያን ቤተክርስትያን አላዳነኝም፡፡
ለኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ያለኝ አክብሮት እንዳውም ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡ ለኦርቶዶክስ ቤተክትስትያን ያለኝ ፍቅር በጥበብና በማስተዋል በዛ እንጂ አልደበዘዘም፡፡ እኔ የቀመስኩትን ሰላም ሁሉም ሰው እንዲቀምሰው እፀልያለሁ እመሰክራለሁ፡፡  
ለወንድሞቻችን ስንመሰክር የዚህ ቤተክርስተያን አባል ሁኑ ሳይሆን ዳግመኛ ተወለዱ ሰው ዳግመኛ ካለተወለደ በስተቀር የቤተክርስትያነ አባልነቱና ፣ ሃይማኖቱና የመፅሃፍ ቅዱስ እውቀቱ የእግዚአብሄርን መንግስት እንዲያይና ብሎም እንዲገባባት አያስችለውም ብለን ነው የምንናገረው፡፡  
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
እንዲያውም እውነተኛው አገሪቱን የሚለውጥ የእግዚአብሄር የወንጌል እንቅስቃሴ ሲመጣ ሊነካ የሚገባው የኦርቶዶክስ ቤተክርስተያንን ነው፡፡ ብዙ ሚሊየን አባላት ያላት ቤተክርስትያን በእግዚአብሄር የመንፈስቅዱስ እሳት ካልተነካች የአገሪቱ በወንጌል መነካት ሙሉ አይሆንም፡፡
ለዚህም ነው እግዚአብሄር በየጊዜው በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ እሳት የሚያስነሳው፡፡ እውነት ነው አንዳንዶች የቤተክርስትያኒቱ መሪዎች በተለያየ ምክኒያት ይህንን የወንጌል እሳት አይፈልጉትም፡፡ እውነት ነው አንዳንድ የቤተክርስተያኒቱ መሪዎች ካለእውቀት በሆነ ቅናት ወንጌሉን በትክክል የተረዱትን ዳግመኛ የተወለዱትን ሰዎች መናፍቃን እያሉ እንደሚያሳድዱና ብሎም ከቤተክርስትያንንም እንደሚያባርሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ንፁሁን ወንጌል የሚያስተምረኝ ቢኖር ኖሮ እና መናፍቅ በመባል ስደት ባይመጣብኝ ኖሮ ወደ ወንጌላዊያን አብያተ ክትስትያናት መሄድ አያስፈልገኝም ነበር፡፡ ባለሁበት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እማርና አድግ ላለሁበት ለኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በረከት መሆን እችል ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡
እግዚአብሄር ህዝቡን ይወዳል፡፡ የእግዚአብሄርን እሳት ግን ሊያግድ የሚችል ምንም የሰው ክንድ የለም፡፡ እኛም ለኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መነሳት እንፀልያለን፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እንወዳለን፡፡
ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እግዚአብሄር ይባርክ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ #በክርስቶስ #መንፈስ #ሃይማኖት #ድንግል #ማርያም #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ከፍታ

No comments:

Post a Comment