Popular Posts

Thursday, March 22, 2018

ሁልጊዜ በጌታ የመደሰት አስራ ሁለቱ ዋና ዋና ምክኒያቶች

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
እኛ በኢየሱስ አዳኝነት ላመንንና ክርስቶስን ለምንከተል ሁላችን ደስ መሰኘት የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ደስ ላለመሰኘት ምክኒያት የለንም፡፡  ደስ ላለመሰኘት አንዳች ምክኒያት ልናገኝ አንችልም፡፡ ስለዚህ ነው ሁሉ ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለውን ትእዛዝ መተግበር ያለብን፡፡ 
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለውን ትእዛዝ ለመፈፀም ብዙ ምክኒያቶች አሉ፡፡ እንዲያውም በጌታ ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ የሚለውን ትእዛዝ ላለመፈፀም በቂ ምክኒያት ልናገኝ እንችልም፡፡
እውነት ነው ዙሪያችንን ስንመለከት ደስ የማይሉ ነገሮች ልናገኝ አንችላለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ እያሉ ሁልጊዜ በጌታ ደስ እንዲለን ይጠበቅብናል፡፡
ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ሊለን የሚገባን ብዙ ምክኒያቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ፅሁፍ ያዘጋጀሁትን አስራ ሁለቱን ምክኒያቶች እነሆ፡፡
ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ሊለን የሚገባን 12ቱ ዋና ዋና ምክኒያቶች
1.      ካለምክኒያት በሚወደው ፍቅር በሆነው በእግዚአብሄር ተወደናል፡፡
እግዚአብሄር የወደደን ሃጢያተኞችና ጠላቶች ሆነን ነው፡፡ አሁንም እግዚአብሄ የሚወደን ስለወደደን ነው፡፡ አንድ ነገር ስናደርግ የሚጠዓን ሌላ ነገር ስናደርግ የሚወደን እግዚአብሄር አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ፍፁም ፍቅር ነው፡፡ ከዚህ ከአግዚአብሄ ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡
እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ 8፡33-35
2.     የሃጢያታችን እዳ ሙሉ ለሙሉ ተከፍሎዋል፡፡
በኢየሱስ የመስቀል ስራ ሙሉ ለሙሉ ከእግዚአብሄ ጋር ታርቀናል፡፡ እግዚአብሄር አሁን በእኛ ደስተኛ ነው፡፡ ሃጢያታችንን ፈፅሞ አያስበውም፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች አድርጎናል፡፡ እንዲያውም ሌሎች ከእግዚአብሄር ጋር የሚታረቁበትን የማስታረቅ ቃል አኑሯል፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡19
3.     አዲስ ፍጥረት ሆነናል፡፡ የዘላለም ህይወት ተሰጥቶናል፡፡
ከዚህ ቀደም ሃጢያትን እንዳልሰራን ያህል እግዚአብሄር ተቀብሎናል፡፡ በቤተሰብ ውስጥ አሁን እንደተወለደ አዲስ ልጅ ተቀብሎናል፡፡ ስንሞት ደግሞ ወደየት እንደምንሄድ እናውቃለን፡፡  
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17
ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። ዮሃንስ 14፡1-3
4.     የእግዚአብሄር መንፈስ የሚኖርብን የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ ሆነናል፡፡
በምድር ላይ እንዲከናወንልን የሚያስፈልገውን ጥበብና ሃይል የሚሰጠንን መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል፡፡ ሁልጊዜ እንዲረዳን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ይኖራል፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ ማደሪያ ቤተመቅደስ ሆነናል፡፡  
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16
5.     እግዚአብሄር እረኛችን ነው የሚያሳጣንም ነገር የለም፡፡
እግዚአብሄር እረኛችን ነው፡፡ እግዚአብሄር እየመራን አንደሆነ ከማወቅ በላይ የሚያስፈነጥዝ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር እረኛችን ሆኖ የምናጣው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም አሁን የሌለን ነገር ሁሉ ቢያንስ ቢያንስ ለአሁን የማያስፈልገን ስለሆነ ብቻ ነው፡፡  
መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡11
6.     እንድናሸንፍ ተወስኗል
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሰራው ስራ አሸናፊዎች ተደርገናል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጠበቅ ውጤት የለም፡፡ ከአሸናፊ ቤተሰብ ከእግዚአብሄር በመወለዳችን አሸናፊ ተደርገናል፡፡ ሌሎችን የሚያሸንፉ አሸናፊዎች እኛ ግን አያሸንፉንም፡፡
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡37
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
7.     ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡
እግዚአብሄርን መስሎ ለመኖር የጎደለብን ነገር የለም፡፡ መንፈሳዊ ለመሆን የሚጠይቀው ነገር ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡ እንዲሁም በምድር ላይ ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3
8.     ከሃጢያት የምንነፃበት መንገድ ተዘጋጅቶዋል፡፡
ሃጢያት ብንሰራ እንኳን በንስሃ ሃሳባችንና መንገዳችንን እንደለወጥን የኢየሱስ ደም ክርስቶስ ደም ከሃጢያታቸን ሁሉ ሊያነፃ የታመነ ነው፡፡
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ ዮሐንስ 1፡9
9.     እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡
እግዚአብሄርበሰማያት ከፍ ያለ ቦታ የሚኖረው ሊረዳን ነው፡፡
ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡26-27
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ሮሜ 8፡31
10.    የመለኮት ባህሪ ተካፋዮች ተደርገናል
የእግዚአብሄር መለኮታዊ ባህሪ ተካፋዮች ተደርገናል፡፡
ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡4
11.     ኢየሱስ ሊመራንና ሃይል ሊሆነን በውስጣችን ይኖራል
እግዚአብሄር ለጠራን ለማንኛውን ጥሪ ብቁ የሚያደርገን ኢየሱስ በልባችን ይኖራል፡፡
በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡9-10
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5
12.    እግዚአብሄር  ለእኛ ህይወት ሙሉ እቅድ አለው፡፡
እያንዳንዳችን  ስለ ህይወታችን የምናውቀው እውቀት ቢኖርም ማናችንም ሙሉ እውቀት የለንም፡፡ እግዚአብሄ የፈጠረን በአላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር ግን የህይወታችን እቅዱና ንድፉ በእጁ ነው ያለው፡፡ እንዲያውም እግዚአብሄር ወደዚህ ምድር እንድንመጣ ያደረገው ያንን እቅድ እንድንፈፅም ነው፡፡ እኛ ባንረዳውም እግዚአብሄር ግን በህይወታችን ንድፍ ላይ በትጋት እየሰራ ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment