Popular Posts

Follow by Email

Friday, March 2, 2018

ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ

የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ኤፌሶን 3፡18-19
ፍቅር የመልካምነቶች ሁሉ መሰረት ነው፡፡ ፍቅር የብርታት ሁሉ መገኛ ምንጭ ነው፡፡ ፍቅር የመልካም ነገሮች ሁሉ ስር ነው፡፡
ስራችን ከፀና ሁለንተኛችን ይፀናል፡፡ ስራችን ከፀና ቅጠላችን ይፀናል፡፡ ስራችን ከፀና ግንዳችን ይፀናል፡፡ ስራችን ከፀና ቅርንጫፋችን ይፀናል፡፡ ስራችን ከፀና ፍሬያችን ይፀናል፡፡
መሰረት የሁሉም ነገር ጅማሬ ነው፡፡ የህንፃ ታላቅነት የሚታየው በመሰረቱ ነው፡፡ መሰረት የሌለው ህንጻ በማንኛውም ጊዜ እንደሚፈርስና እንዲያውም ህንፃው እንደሌለ ይቆጠራል፡፡
ለህይወታችንም ይሁን ለአገልግሎታችን መሰረት ሊሆን የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ የህይወት መሰረት ፍቅር ነው፡፡ የእኛ ስር የሚፀናው በሃብት ፣ በዝና ፣ በእውቀት ወይም በሃይል ሳይሆን በፍቅር ነው፡፡
በብቸኝነት ፍቅርን ማወቅ አንችልም፡፡ ከሰው ጋር ካልተቀላለቅልን ፍቅርን በሃሳብ እንጂ በተግባር ልንረዳ አንችልም፡፡ የእኛ ስርና መሰረት በፍቅር የሚፀናው ደግሞ ፍቅርን ከቅዱሳን ጋር ስንለማመደው ብቻ ነው፡፡
ሰው ለብቻው ፍቅርን አይለማመድም፡፡ ሰው የማይወደድ ሰው ሳያጋጥመው ፍቅርን ሊለማመድ አይችልም፡፡ ሰው የሚበድለው ሰው በሌለበት ፍቅርን ሊማር አይችልም፡፡ ሰው ከእርሱ የተለየ የሚያስብ ሰው በሌለበት ፍቅርን ሊያዳብር አይችልም፡፡
የሰው ፍቅር በፀሎት ቦታ አያድግም፡፡ ሰው ላለመጎዳት ራሱን ባገለለበት ቦታ ፍቅሩ አያድግም፡፡ ሰው ፍቅርን በፀሎት ቦታ አያውቀውም፡፡ የሰው ፍቅር በመልካም ሰዎች መካከል አይፈተንም፡፡ የሰው ፍቅር በመልካም ሰዎች መካከል አይሞረድም፡፡ የሰው ፍቅር በሚስማሙት ሰዎች መካከል አያድግም፡፡ 
አስቸጋሪን ሰው ስታይ ነው አንተ ለእግዚአብሄር ምን ያህል አስቸጋሪ ልትሆን እንደምትችል የምትረዳው፡፡ አስቸጋሪ ሰው ስታይ ነው እግዚአብሄር ስንቱን አስቸጋሪ ሰው እንደተሸከመ የምትረዳው፡፡ ትግስትን የሚፈትን ሰው ሰው ሲያጋጥምህ ነው የእግዚአብሄርን ፍቅር ክብር የምትረዳው፡፡ ግራ ሰው ሲያጋጥምህ ነው ይህን የተሸከመውን እግዚአብሄርን በፍቅሩ ልትመስለው የምትፈልገው፡፡ ከአንተ ፍፁም የተለየ ሰው ሲያጋጥምህ ነው እግዚአብሄርን ስለፍቅሩ የምታደንቀው፡፡ እኔ ብሆን አብሬው እኖራለሁ የምትለው ሰው ሲያጋጥምህ ነው ይህንን ሰው በተሸከመው በእግዚአብሄር ፍቅር ይበልጥ የምትተማመነው፡፡
ትግስት ፈታኝ ሰው በሌለበት ትግስትን እንዴት እናደርጋለን? ቸርነትን የሚጠይቅ ሁኔታ ሳያጋጥመን ቸር መሆናችን እንዴት ይታያል? የሚያስቀና ሰው ሳናይ እንደማንቀና በምን እርግጠኛ እንሆናለን? የፍቅር ሰው መሆናችንንና እንደማንመካ ለማወቅ የሚያስመካ ነገር ይጠይቃል፡፡ የፈለግነውን እንድናደርግ የሚፈትን ሁኔታ ሳያጋጥም የማይገባንን እንደማናደርግ በምን እርግጠኛ እንሆናለን? የራሳችንን ለመፈለግ ሳንፈተን የራሴን አልፈልግም ብለን እንዴት በድፍረት መናገር እንችላለን? በፍቅር ማደጋችንን እና እንደማንበሳጭ ለመወሰን  ከሚያበሳጭ ሰው ጋር ኖረን አለመበሳጨታችንን ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የሚበድል በሌለበት በደልን አለመቁጠራችንን እንዴት እናረጋግጣለን? 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4-5
ፍቅርን የምትማረው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው፡፡ በፍቅር የምትሰለጥነው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው፡፡ በፍቅር የምታድገው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው፡፡
የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ኤፌሶን 3፡18-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #ስር #መሰረት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ከቅዱሳንሁሉጋር #መታበይ #መመካት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment