Popular Posts

Tuesday, March 13, 2018

ውብ አድርጎ

ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። መክብብ 3፡11
አንዳንድ ጊዜ ህይወታችን ብትንትን እንዳለ ይሰማናል፡፡ አሁን ይህ ብትንትን ያለ ህይወት ቅርፅ ያገፅ ይሆን ብለን እናስባለን፡፡ ህይወታችንን ምኑን ከምኑ እንደምናያይዘው ግራ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ መታገስ ሃይላችንን በከንቱ እንዳናባክን የሚያደርግ ሃይል ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጊዜ መጠበቅ ብዙ ዘርተን ጥቂት እንዳናጭድ ያድነናል፡፡
መኪና የተሰራው ለመነዳት እንጂ ለመገፋት አይደለም፡፡ ሰው መኪናውን መንዳት ትቶ ሁሌ ቢገፋው ጉልበቱን በከንቱ ያባክናል፡፡ ከእግዚአብሄር ጊዜ ውጭ የምናደርገው ነገር መኪናን እንደ መግፋት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚበልጥ ከባድ ስራ ነው፡፡   
ጊዜው ሲሆን ግን እነዚህን ምልክቶች ያሳያል፡፡
በእግዚአብሄር ጊዜ የሆነ ነገር ውበት አለው
የእግዚአብሄር ጊዜ እስኪመጣ መታገስ ይጠይቃል እንጂ የእግዚአብሄር ጊዜ ሲመጣ ግን ሁሉ ነገር ቅርፅ ይይዛል፡፡
በእግዚአብሄር ጊዜ የሆነ ነገር ይሰካካል
የእግዚአብሄር ጊዜ ሳይመጣ ብናወጣው ብናወርደው እንዴት እንደሚሆን ግራ ግብት ያለን ነገር የእግዚአብሄር ጊዜ ሲመጣ ነገሮች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ እየሄዱ ለተፈፃሚነቱ በትጋት ይሰራሉ፡፡  
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28
በእግዚአብሄር ጊዜ የሆነ ነገር ሁሉም ነገር ወደ አንድ አቅጣጫ ያመራል፡፡ ሁሉም ነገር ለተፈፃሚነቱ ይሰራል፡፡ በመንገድ ላይ የሚቆም እና የሚቋቋም ምንም ሃይል አይኖርም፡፡
እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ሮሜ 8፡31
ድፍረቱም እምነቱም ይመጣል
አሁን ቁጭ ብለን ወደፊታችንን ብናስበው የሚያስፈራን ነገር በጊዜ ግን ለጊዜው የሚሆን እምነት ስለሚኖረን በድፍረት እናከናውነዋለን፡፡ ስለዚህ ነው ዛሬ ላይ ሆናችሁ ስለነገ አትጨነቁ፡፡ ነገ የራሱን መፍትሄ ይዞ ይመጣል የሚለው፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34
እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር። ገላትያ 3፡23
እረፍትና እርካታ አብሮት ይመጣል
የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም። ምሳሌ 10፡22
ወደፊቱም እስተማማኝ ነው
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። መክብብ 3፡11
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

No comments:

Post a Comment