ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ዕብራውያን 3፡12
የልብ ጥንካሬ ምንድነው?
የልብ ጥንካሬ የራስን ነገር ብቻ መፈለግ ነው፡፡ የልብ ጥንካሬ ራስ ወዳድነት ነው፡፡
የልብ ጥንካሬ አለመመለስ ነው፡፡ የልብ ጥንካሬ አንገተ ደንዳናነት ነው፡፡
የልብ ጥንካሬ ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን ነው፡፡ የልብ ጥንካሬ የዋህ አለመሆን ነው፡፡
የልብ ጥንካሬ ትእቢተኝነትና ማን አለብኝነት ነው፡፡
የልብ ጥንካሬ እልከኛነት ነው፡፡
ኢየሱስ ሚስትን መፍታት ይቻልና አይቻል እንደሆነ ስለፍቺ ሲጠይቁት እርሱ ግን ስለፍቺ ሳይሆን ስለፍቺ መንስኤ ፣ ፍቺ ከየት እንደሚመጣና የፍቺ ምንጭ ምን እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ፍቺ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ፍቺ የሌላ የከፋ ችግር ምልክት ነው፡፡ የልብ ጥንካሬ እግዚአብሄር ያጣመረውን የሚለይ ከሆነ ሌላ የማያደረገው ምን ክፉ ነገር አይኖርም፡፡ ችግሩ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ችግሩ የልብ ጥንካሬ ነው፡፡ ችግሩ በዚህና በዚያ አይፈታም፡፡ የፍቺ ችግር የሚፈታው የልብ ጥንካሬ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው፡፡ የልብ ጥንካሬ ችግር ከተፈታ የሚቀር ሌላ ምንም ችግር አይኖርም፡፡ የልብ ጥንካሬ ችግር ሲፈታ የፍቺ ችግር አብሮ ይፈታል፡፡
እርሱም፦ ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። ማቴዎስ 19፡8
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። ማርቆስ 10፡5
የልብ ጥንካሬ እግዚአብሄር ክቡር ነው ያለውን ትዳርን ያዋርዳል፡፡
መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ዕብራውያን 13፡4
የልብ ጥንካሬ እግዚአብሄር መልካም ነው ያለውን ክፉ ያደርጋል፡፡
እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍጥረት 2፡18
የልብ ጥንካሬ ክቡሩን ቃልኪዳን ያዋርዳል
እናንተም፦ ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው። ሚልክያስ 2፡14
የልብ ጥንካሬ የእግዚአብሄርን እርዳታ ያግዳል
በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። ማቴዎስ 13፡15
የልብ ጥንካሬ ከእግዚአብሄር ህይወት ያርቃል
እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ኤፌሶን 4፡18
መጠንቀቅ እንጂ የልብ ጥንካሬ ሊደርስብኝ አይችልም የሚል ማንም ሰው የለም፡፡ ልብ አንዴ አስተካክዬዋለሁ ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ ልብ በየጊዜው ሊፈተሽ የሚገባው እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤ እየተባለ፦ ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ዕብራውያን 3፡12-15
ለልብ ጥንካሬ ዛሬ የመስማት ፣ የመለወጥና የመቀየር ተስፋ አለ፡፡
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፦ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ዕብራውያን 3፡7-9
ልበ ጠንካራ ሰው ካልተመለሰ በስተቀር እረፍትን አያይም
በዚህ ስፍራም ደግሞ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም። እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ዕብራውያን 4፡5-7
የልብ ጥንካሬ የእግዚአብሄርን ቁጣ ይጋብዛል
ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። ሮሜ 2፡5
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #ልብ #የልብጥንካሬ #ንስሀ #መመለስ ##መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment