Popular Posts

Tuesday, March 6, 2018

የህይወት ጭላጭ

አንድ ቀን አዘውትረን ቡና የምንጠጣበት ቦታ ላይ ቡና የምትሰራልንን ሴት ጌታን ትከተያለሽ ወይ ቤተክርስትያን ትሄጃለሽ ወይ ብዬ ጠየቅኳት፡፡  
ገልመጥ አደረገችኝና እንዴ በዚህ እድሜዬ?! አለች በመገረም፡፡ ቀጠለችና እድሜዬ ትልቅ ሲሆን ሳረጅ እንጂ በዚህ እድሜዬና ቤተክርስትያን ቤተክርስተያን አልልም አለች፡፡ በጣም ተገርማ ተመለከተችኝና አሁን እንደማታደርገው ልታደርገው እንዳልተዘጋጀት ገለፀችልኝ፡፡ እኔ ደግሞ አንቺ እግዚአብሄር ኩሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር የህይወትሽን ዋና ጊዜ እንጂ ጭላጩን አይፈልግም አልኳት፡፡
እግዚአብሄ ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ኩሩ ንጉስ ነው፡፡
እግዚአብሄር መውሰድ የሚፈልገውን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ዋናውን ስለሆነ የሚጠብቀውም ዋናውን እንድንሰጠው ነው፡፡
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
እግዚአብሄር የሰጣችሁትን ዝም ብሎ የሚወስድ የኔ ቢጤ አይደለም፡፡
እግዚአብሄ ስጦታን ከመቀበሉ በፊት ሰጭውን ያያል፡፡ እግዚአብሄር የስስታምን ምግብ አይበላም፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። ምሳሌ 23፡6-7
ለእግዚአብሄር ገንዘብህን ጊዜህን ጉለብተህን እውቀትህን ስትሰጥ እግዚአብሄር አስቀድሞ ልብህን ያያል፡፡ እግዚአብሄር የምንም ነገር ችግር የለበትም፡ምንም ነገር ቢሆን ለእግዚአብሄር በደስታ ካልሰጠኸው አይቀበለውም፡፡
እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7
ኢየሱስ አንዱን ተከተለኝ ሲለው እሺ እከተልሃለሁ ችግር የለም ነገር ግን አሁን አይደለም አሁን ቢዚ ነኝ አሁን የምሰራቸው አስፈላጊ ስራዎች አሉ ያንን ስጨርስ ግን እከተልሃለሁ ችግር የለም ያለው ይመስላል፡፡ ኢየሱስ እንኳን እሺ ብቻ አልክ ዋናው እሺ ማለትህ ነው ችግር የለም በፈለግህ ጊዜ መጥተህ ትከተለኛለህ አላለውም፡፡ ይሄ የሚለውን ሁለ እንዲተወውና ወንጌልን እንዲስብክ ነው የነገረው፡፡
ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው። ኢየሱስም፦ ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው። ማቴዎስ 8፡21
እግዚአብሄር ሰውን ይወዳል፡፡ እግዚአብሄር ግን ማንንም አይለምንም፡፡ እግዚአብሄር ማንንም ለመለመን ክብሩ አይፈቅድለትም፡፡ እግዚአብሄርን የምንከተለው ለራሳችን ብለን ነው፡፡
ኃጢአት ብትሠራ ምን ትጐዳዋለህ? መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ? ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል? ኢዮብ 35፡6-7
ሌላው ደግሞ እንዲሁ እከተልሃለሁ ነገር ግን ቤተሰቦቼን ልሰናበት አለው፡፡ ቤተሰብን መሰናበት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሄር ነገር የምናስበልጠውን ምንንም ነገር እግዚአብሄር በቀላሉ አይመለከተውም፡፡
ደግሞ ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው። ሉቃስ 9፡61-62
እግዚአብሄር በህይወታችን አንደኛ ካልሆነ ምንም ሌላ ደረጃ አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር አንደኛውን ካልሰጠኸኝ ተወው ይቅርብኝ ነው የሚለው፡፡
ስለዚህ ነው በአገራችንም ትልቅ ሰው ጌታን ሲቀበል እርስዋ ቤተክርስትያን በመሳሚያ ጊዜዋ ጴንጤ ሆነች የሚባለው፡፡ በእነርሱ አመለካከት ሰው ለእግዚአብሄር የሚያድረው የራሱን ህይወት ጨርሶ በህይወቱ የድካም ጊዜ ነው፡፡ ሰው ጌታን የሚያገለግለው በዋናው ህይወቱ ሳይሆን በጭላጩ ነው፡፡
የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። ዘፀአት 20፡7
ለዚያም ነው ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ያለው፡፡ ኢየሱስ ከጌቶች ጋር አብሮ መቆጠር አይፈልግም፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
ለዚያም ነው ጌታ ክርስቶስን ለዩት ቀድሱት ከሌላ ጋር አትቀላቅሉት ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡14-15
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ኩሩ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው የመጀመሪያውን ነው፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሄርን ስራ በቸልታ የሚሰራ እርጉም ይሁን የሚለው፡፡
የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደግ ርጉም ይሁን፥ ኤርሚያስ 48፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #አምላክ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #መታመን #ፍርሃት #ብቸኛአምላክ #መስዋእት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment