Popular Posts

Saturday, March 10, 2018

አትድከም

ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። ምሳሌ 23:4
ባለጠጋ ለመሆን አትቆጣጥብ፡፡ እግዚአብሄር ባለጠጋ የሚያደርግህ የቤት ኪራህን ገንዘብ ተጠቅሞ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ባለጠጋ የሚያደርግህ የምግብህን ገንዘብ ቀንሶና ያንን አጠራቅሞ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ባለጠጋ የሚያደርግህ እየበላህ እየጠጣህ የቤት ኪራይህን እየከፈል ኑሮህን እየኖርክ ነው፡፡ እየበላህ እየጠጣህ ካልሆነ ባለጠጋ ያደረገህ እግዚአብሄር ሳይሆን አንተ በራስህ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡
ባለጠጋ ለመሆን በሳንቲም የምትጣላ ከሆንክ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ በክፍፍልና በድርድር ጊዜ የሳንቲም ማለፍ እረፍት የሚነሳህ ከሆንክ ለእውነተኛ ባለጠግነት ዝግጁ አይደለህም፡፡ የሳንቲምን ወደሌላው ማለፍ የሚያንገበግብህ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ ከእኔ ይለፍ ችግር የለም ባለጠጋ የሚያደርግ እግዚአብሄር ነው ካላልክ በስተቀር ባለጠጋ ለመሆን በከንቱ አየደከምክ ነው፡፡  
አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። መዝሙር 14፡22-24
እግዚአብሄር እንዲያበለፅግህ እየረዳኸው እንደሆነ ከተሰማህ ባለጠጋ ለመሆን በከንቱ እየደከምክ ነው፡፡ በፋራም በአራዳም ብለህ እንደምንም ብለህ ሃብታም ለመሆን እየሞከርክ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ ዘና ማለትን ኑሮን ማጣጣም ካቆምክ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡
ባለጠጋ ለመሆን በውሸት እግዚአብሄርን የምትረዳው የሚመስልህ ከሆነ እውነትን የማትናገርለት ነገር የአንተ ሃብት አይደለምና ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚባርክህ በክብር ነው እንጂ በውርደት አይደለም፡፡
አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19
ባለጠጋ ለመሆን ተንኮል ውስጥ የምትገባ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ የእግዚአብሄር በረከት ንፁህ ነች፡፡
የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም። ምሳሌ 10፡22
እጅህ ተንቀጥቅጦ ለጥቂት የምታገኘው ሃብት የአንተ ሃብት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ሃብት ፈልጋ የምታገኝህ እንጂ ፈልገህ ልታመልጥህ ስትል ለጥቂት የምታገኛት ሃብት አይደለችም፡፡
ለሊቱን ሙሉ እየተጨነክና እንቅልፍ እያጣህ የምታገኘው ሃብት ያንተ አይደለም፡፡ ሰላምህንና ደስታህን ሁሉ የምትሰዋበት ሃብት አይፈለክ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ ሰጥተህም በትነህም የእግዚአብሄር በረከት ተመልሶ የሚመጣ እንጂ እንደምንም የምታቆየው የማይያዝ የማይጨበጥ ምትሃት አይደለም፡፡
በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡8-9
በፈንጂ ላይ እንደመራመድ ተጨንቀህና ተጠበህ ሃብታም ለመሆን እየሞከርክ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡
እንድምንም ለጥቂት እንደ ሎተሪ እንደ እድል የሚደርስህ ሃብት እየፈለክ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን እየደከምክ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ባለጠግነት ሰፋ ያለች አልማ የማትስት ሰፊ በረከት እንጂ የእድል ጉዳይ አይደለችም፡፡  
አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። መዝሙር 18፡36
ሰውን ይቅር ስላልከው እውነተኛ እንደሆነ ያረጋገጥክለት ከመሰለህ እያረፍክ አይደለህም፡፡ ሰውን ይቅር ካልከው ይከናወንለታል ብለህ ካሰብክ የማይገባህ የፍርድ ወንበር ላይ እየተቀምጥክ ነው፡፡ ሃላፊነትህ ይቅር ማለት እንጂ እንዳይከናወንለት ብትቋጥርም የሚከናወንለት ሰው ይከናወንለታል፡፡
ያጠፋ ሰው እንዲቀጣ እግዚአብሄርን አትርዳው፡፡ እግዚአብሄርን ልትረዳው ከፈለክግክ ነገር ታበላሻለህ፡፡ ያንተ ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ አይሰራም፡፡ ሰውን አትቅጣ ፡፡ ሰውን ይቅር በል ፍታ ልቀቅ እንጂ ሰውን እትቅጣ፡፡ ሰውን ካልቀጣኸው የማይቀጣ ከመሰለህ ፍትህን ለማምጣት የእግዚአብሄርን ቦታ እየወሰድክ አላግባብ እየደከምክ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
አንተ እንዲከናወንልህ በአካባቢህ ያሉ ሰዎች ሁሉ መውደቃቸውን የምትጠብቅ ከሆንክ በራስህ ለመከናወን እየደከምክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በረከትን የሚሰጥህ ከሌላው ልጅ ነጥቆ እንደሆነ ከተሰማህ በራስህ ጉልበት ለመባረክ እየሞከርክ ነው፡፡ የሌሎች ብርሃን መጥፋት ያንተን ብርሃት የሚያጎላው ከሆነ ራሰህን ለማንሳት እየደከምክ እንጂ እግዚአብሄር እያነሳህ አይደለም፡፡
ሰው ለማስተካከል ጉልበትህን የምትጠቀም ከሆንክ በከንቱ እየደከምክ ነው፡፡ ያለህ ሃላፊነት የእግዚአብሄርን ቃል መንገር እንጂ ሰውን መለወጥ አይደለም፡፡ ሰውን ለመለወጥ ቃሉን እያጋነንከው ከሆነ ሰውን እግዚአብሄር እንዲለውጠው እድል እየሰጠህ ሳይሆን በራስህ ሃይል በሰው ክንድ ሰውን ለመለወጥ እየደከምክ ነው፡፡
ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና። 2ኛ ዜና 32፡8
እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ። መዝሙር 127፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አገልጋይ #እረፍት #ድካም #ጥረት #ልፋት #ትህትና #መልካምነት #መከባበር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ውድድር #ፉክክር #ዋጋ

No comments:

Post a Comment