Popular Posts

Wednesday, March 28, 2018

ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል

ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል። ምሳሌ 16፡32
በምድር ላይ ሃያል የሆኑ ግን ለምድር በረከት ያልሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በምድር ላይ ባለጠጋ የሆኑ ነገር ግን ለምድር ስጋት የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በምድር ላይ ጥበበኛ የሆኑ ነገር ግን የምድር አደጋ የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡
ሰው ሃይሉን ለክፋትም ይሁን ለበጎነት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ሃይላችንን ለምን እንደምንጠቀምበት እስካልታወቀ ድረስ ሃይል አለን ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሃይል በማን እጅ እንዳለ ካልታወቀ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ሃይልን ብቻ አይተህ ከተመኘኸው ሃይል ያለውን የጥፋት አቅም አልተረዳህም ማለት ነው፡፡
ሰው ባለጠጋ ነው ማለት ባለግነቱን ለክፋት እንደማይጠቀምበት ካልተረጋገጠ በስተቀር ባለጠግነቱን ብቻ የሚመኙት ነገር አይደለም፡፡ ሰው ባለጠግነቱን ለመልካም ነገር ብቻ ሳይሆን ሰውን ለመግደል ለማጎሳቆል ለመበዝበዝ ለማስለቀስ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
ሰው ጥቢብ ነው ማለት ጥበቡን ለክፋት አይጠቀምበትም ማለት አይደለም፡፡ ጥበብ አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥበብ በረከት ሊሆን ይችላል፡፡ ጥበብ እንደሚይዘው ሰው ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡
ሃያልነት ባለጠግነትና ጥበብ ከውጭ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ሃያልነት ባለጠግነትና ጥበብ የሚያስመኩ የእድገት መለኪያዎች አይደሉም፡፡ ሃያልነት ባለጠግነትና ጥበብ የሰውን ማደግ መለወጥና መልካምነት አያሳዩም፡፡
ለሰው ሃያልነትን የሚሰጠው እግዚአብሄር ነው፡፡ ሰውን ከባለጠግነት ጋር የሚያገናኘው የእግዚአብሄር አሰራር ነው፡፡ ለሰው የጥበብን አእምሮ የሚሰጠው እግዚአብሄር ነው፡፡ ሃያልነት ባለጠግነትና ጥበብ ሃያሉን ባለጠጋውንና ጠቢቡን የሚያስመካው ምንም ነገር የለም፡፡
በመርህ መኖር ግን የሰውን የባህሪ እድገት ይጠይቃል፡፡ ትእግስት ግን የሰውን መለወጥ ይጠይቃል፡ትእግስት ግን የተሻለ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ትእግስት ግን ራስን መግዛትን ይጠይቃል፡፡
ሰው ሃያልነቱ የሚለካው ራሱን ሲገዛ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሃያልነቱ የሚለካው ማድረግ የሚፈልገውን ሲያደርግ ፣ ማድረግ የማይፈለገውን ሳያደርግ ነው፡፡ የሰው ሃያልነት የሚለካው ሰው በራሱ ላይ ሙሉ ስልጣን ሲኖረው ነው፡፡ የሰው ሃያልነቱ የሚለካው ራሱን ሲመራ ብቻ ነው፡፡  
ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በውስጡ ባለጠጋ ሲሆን ነው፡፡ ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በሰላም ፣ በደስታ ፣ በእረፍትና በእርካታ ባለጠጋ ሲሆን ነው፡፡ ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በነፍሱ ባለጠጋ ሲሆን ነው፡፡
ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። 3ኛ ዮሐንስ 1፡2
ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በይቅርታና እና በምህረት ባለጠጋ ሲሆን ነው፡፡ የሰው ባለጠግነት የሚለካው ለራሱ ነገሮችን በራስ ወዳድነት በማግበስበስ ሳይሆን በመልካም ስራ ባለጠጋ ሲሆን ነው፡፡
እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ  ጢሞቴዎስ 6፡18-19
ሰው ጠቢብነቱ የሚታወቀው እግዚአብሄርን በመፍራት ከእግዚአብሄርና ከሰው ጋር በትግስትና በትህትና ሲኖር ነው፡፡ ሰው ጠቢብነቱ የሚታወቀው በመጀመሪያ ከፈጠረው ጋር እንዴት በትህትና እንደሚኖር ሲያውቅ ነው፡፡ ሰው ጠቢብነቱ የሚታወቀው በህይወቱ እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ለፈጠረው ለሰራው ለእግዚአብሄር እውቅና መስጠቱ ነው፡፡ ሰው ጠቢብነቱ የሚለካው ለእግዚአብሄር የመጀመሪያውን ስፍራ ሲሰጥ ነው፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። ምሳሌ 1፡7
ስለዚህ ነው ትእግስተኛ ሰው ከሃያል ስው ይሻላል የሚባለው፡፡
ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል። ምሳሌ 1632
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment