እግዚአብሄር ባለጠጋ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ለመባረክ ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን በሚባርከው በረከት ሰው ተጠቃሚ እንዲሆን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ሰውን የሚባርከው በረከት እንዲባክን እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን በረከት በትክክል እንዲያስተዳድረው እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
ሰው የተሰጠውን በረከት በትክክል ካላስተዳደረ ያባክነዋል፡፡ ሰው የተሰጠውን በረከት የሚይዝበት ትክክለኛ አያያዝ ከሌለው በረከቱ ይባክናል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን ከመባረኩ በፊት የበረከቱን አስተዳዳሪውን ሰውን መስራቱን የሚያስቀድመው በዚህ ምክኒያት ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለበረከቱ ሳይሆን ስለአስተዳሪው መሰራት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና የሚያስቀድመው አስተዳዳሪው ሰው ከተሰራ በረከቱን በትክክል ማስተዳደር እንደሚችል እግዚአብሄር ስለሚያውቅ ነው፡፡ አስተዳደሪው በሚገባ ከተሰራ በረከቱን ለታሰበው አላማ ሊያውለው ይችላል፡፡
ስለዚህ ነው ሰውን ከመባረኩ በፊት እግዚአብሄር የሰውን ታማኝነት የሚመዝነው፡፡ አስተዳደሪው ታማኝ ከሆነ በረከቱ ለታለመለት አላማ ይውላል፡፡ አስተዳደሪው ታማኝ እስካልሆነ ደርስ ግን ሰው ምንም ቢባረክ በሚያፈስ እቃ ውስጥ እንደተቀመጠ ፈሳሽ በረከቱ ይባክናል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
አስተዳዳሪው ሳይሰራ በፊት የተገኘ በረከት ግን ከእግዚአብሄርም ሊሆን አይችልም እንዲሁም ደግሞ ንፁህ ሊሆን አይችልም፡፡ አስተዳዳሪው ቀስ በቀስ ሳይሰራ በፊት የተገኘ በረከት መሰረት እንደሌለው ቤት ነው፡፡ አስተዳደሪው ሰው በባህሪ ሳይሰራ አስቀድሞ የተገኘ ርስት ፍፃሜው ለመልካም አይሆንም፡፡
በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም። ምሳሌ 20፡21
ስለዚህ ነው ሰው ሃብቱን በትክክል ከማስተዳደሩ በፊት በባህሪ ማደግና ሃብቱን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ብስለት ማግኘት እንዳለበት መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። ገላትያ 4፡1-2
ርስትን ለመቀበል ሰከንድ አይፈጅም፡፡ ነገር ግን ርስትን በትክክል ለማስተዳደር የሚያበቃ ብስለትን ለማግኘት ዘመናት ይጠይቃል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #አስተዳደሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment