Popular Posts

Follow by Email

Thursday, March 22, 2018

የቃልኪዳን በረከቶቻችን

እግዚአብሄር የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር እርሱ ፈቃድ እንዳለው ሁሉ ሰውንም የፈጠረው ፈቃድ እንዲኖረው አድርጎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በፈቃዱ ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ እንዲሰራ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለአብሮ ሰራተኝነት ነው፡፡
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡9
እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው በምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲወክለው ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው እርሱ በሰማይ እንዳለና እንደሚገዛ ሰውም እርሱን ወክሎ በምድር ላይ እንዲገዛ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ለአብሮ ሰራተኛነት ነው፡፡
እግዚአብሄር አብሮን የሚሰራው ደግሞ በመርህ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራው ነገር አለ፡፡ እኛ የምንሰራው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር ሁሉንም ነገር አይሰራም፡፡ እኛም ሁሉንም ነገር አንሰራም፡፡ እግዚአብሄር የማይሰራው ነገር አለ፡፡ እኛም የማንሰራው ነገር አለ፡፡  
በክርስትና እኛ የምንሰራውንና የማንሰራውን ለይተን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በክርስትና እግዚአብሄር የሚሰራልንንና የማይሰራልንን ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ በክርስትና እግዚአብሄር የሚሰራውን ማወቅና ያንን ለመስራት አለመሞከር እንዲሁም እግዚአብሄር የማይሰራውን ማወቅና ያንን ለመስራት መትጋት ውጤታማ ያደርጋል፡፡
እግዚአብሄር ከእኛ ጋር የሚሰራው በቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳን በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ ቃልኪዳን ሁለቱ ወገኖች አንዱ ለሌላው የሚያደርጉትን መስማማት ነው፡፡ ቃልኪዳን ውጤታማ የሚሆነው አንዱ ማድረግ የሚችለውን ነገር ብቻ ሲያደርግ የማይችለውንም ነገር ሌላው እንደሚያደርግ ሲያምን ብቻ ነው፡፡
ቃልኪዳን የሚመሰረተው በመተማመን ነው፡፡ እግዚአብሄር ታማኝ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ልናምነው ይገባል፡፡ ስለዚህ ነው ካለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻለው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
እግዚአብሄር በቃሉ ስለ ቃልኪዳናችን ያለውን ካመንን እንከናወናለን፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ ስለ ቃልኪዳኑ ውል የተናገረውን ካመንና ከተከተልን ይሳካልናል፡፡ እግዚአብሄር ስለ ቃልኪዳኑ ያለውን ካመነን በቃልኪዳን አጋራችን በእግዚአብሄር ሃይል እንኖራለን፡፡ እግዚአብሄር ስለ ቃልኪዳኑ በቃሉ ያለውን ካመንን ለቃልኪዳን አጋራችን እግዚአብሄር ጠቃሚ ሰዎች እንሆናለን፡፡
ለምሳሌ መፅሃፍ ቅዱስ ስለመሰረታዊ ፍላጎታችን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው መሟላት ሃላፊነት ያለበት እግዚአብሄር እንደሆነና እርሱ እነዚህ ነገሮች እንደሚያቀርብ ያስተምረናል፡፡ የእኛ ሃላፊነት ደግሞ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን መፈለግና መፈፀም መሆኑን በተለያየ መልኩ ደጋግሞ ያስተምረናል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33
ስለዚህ የሚያጨንቃችሁን በእርሱ ላይ ጣሉት እርሱ ስለእናንተ ያስባልና በማለት ስለቃልኪዳኑ ድርሻ ያስተምረናል፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
የወደፊት ህይወታችን መጨነቅ እንደሌለብን የህይወት እቅዳችን ሁሉ በእግዚአብሄር ዘንድ እንዳለና የእኛ ሃላፊነት በፀሎት ወደእርሱ በመቅረብ የህይወት እቅዳችንን ተረድተን ያንን መከተል እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ስለቃልኪዳን የስራ ድርሻችን ያስተምረናል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርሚያስ 29፡11-13
እግዚአብሄር ራሱ የቃልኪዳን አጋራችን ስለሆነ ነው እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው ተብሎ የተነገረው፡፡
እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። መዝሙር 33፡12
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃልኪዳን #ድርሻ #የስራክፍፍል #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment