Popular Posts

Monday, June 25, 2018

የምሁራኖቻችን ተግዳሮት

ምሁራን ለአገር እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ የእውቀትና የመረጃ አለም ካለምሁራን ንቁ ተሳትፎ አገር የሚገባውን ያህል ታድጋለች ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
ባደጉት አገሮች በአብዛኛው ፖለቲካና ሙያ ድንበራቸውን አውቀው ተከባብረው ይኖራሉ፡፡ ፖለቲከኛው ዋና ፖሊሲን የሚመለከት ነገር ካልሆነ በስተቀር የሙያውን ስራ የሚተወው ለምሁራኑ ነው፡፡ ምሁራኑም ሙሉ በሙሉ የማይደግፉት ፖሊሲም ቢሆን ከፖለቲካ ውጭ አገሪቱን በሙያቸው ያገለግላሉ፡፡ እኔ የምስማማበት ፖሊሲ ካልገሆነ ብለው ራሳችውን ከሙያው አያገሉም፡፡
ባደጉት አገሮች የአገር መዋቅር በሚገባ ስለተገነባ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ሙያውን ደግሞ ለምሁራኑ የሚሰጥበትና አንዱ ከአንዱ የድንበር መስመር እንዳያልፍ የሚያደርግበት በአመታት የዳበር ስርአት አለ፡፡ ስርአቱ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኛውም በአብዛኛው ድንበሩን አውቆ ወደሙያው ድንበር ዘልቆ የባለሙያውን ቦታ አይገዛም፡፡ ምሁሩም እንዲሁ በአብዛኛው ድንበሩን አውቆ ወደ ፖለቲከኛው ድንበር ሳያልፍ በሙያው ብቻ አገርን ያገለግላል፡፡
በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ግን በዚህ ዘርፍ ትልቅ ተግዳሮት አለ፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ብዙ ፖለቲከኞች ስጋት አለባቸው፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ስልጫን ሲይዝ ከእርሱ የተለየን ሰው ማቅረብ አይፈልግም፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ የሚያምነው ዝለል ሲባል ምን ያህል ከፍታ ልዝለል ብሎ ብቻ የሚጠይቅ ተከታይን ነው፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ በራሱ ስለማይተማመን ከእርሱ ለየት ያለ ሃሳብ የሚያመጣ ሰው ጠላቱ እንጂ ወዳጁ አይደለም፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ራሱን በታማኝ ሎሌዎች ይከባል፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ከስሩ የሚሾመው ሙያ ያለውና በሙያውና በእውቀቱ  ህዝብን የሚያገለግለውን ሳይሆን ለእርሱ ታማኝ ሎሌ የሆነውን በሙያው እውቀት የሌለውን ሰው ብቻ ነው፡፡
ስጋት ባለበት ፖለቲከኛ የተመረጡና የተሾሙ ፖለቲከኞች ለፖለቲካው ታማኝ ሎሌን ብቻ በመሾም ዋናውን መሪ ይከተላሉ፡፡ ስጋት ባለበት ፖለቲከኛ የተሾሙ መሪዎች እንዲሁ ከስራቸው ታማኝ ሎሌ የሆነውን ምንም ጥያቄ ሳይጠይቅ ክፉም ይሁን መልካም የሚታዘዘውን ሰው ከስራቸው ይሾማሉ፡፡ እንደዚህ እያለ ከላይ ለጠቅላይ ሚንስትር እስከ ቀበሌ ከፕሬዝዳንት እስከ ፅዳት ሰራተኛ ድረስ በሙያ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት ይሾማሉ፡፡ ይህ ሲሆን ሙያው ለሙያተኞች ስላልተሰጠ በአገልግሎት እጦት ሳቢያ ህዝብ ይሰቃያል፡፡
በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ተግዳሮት አንዳንድ ስጋት ያለባቸው ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ምሁራኑም ናቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራን የፖለቲካውን ስልጣን ለፖለቲከኛው ለመተው አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ ምሁራን የፖለቲከኛውን እጅ በጉልበት ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ድንበራቸውን አላግባብ ይጥሳሉ፡፡ ይህ ፖሊሲ ካልተለወጠ አገራችንን አናገልግልም ብለው ያኮርፋሉ የግል ድርጅቶችን ያገለግላ ወይም አገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ እውነት ነው አይን ያወጣ ግፍ ሲፈፀም ከፖለቲከኛው ጋር አብሮ ክፋትን መዋጋት ካለተቻለ ከክፋት ጋር ላለመተባበር ራስን ማግለል ወሳኝ ነው፡፡
ነገር ግን አብሮ መስራት ውስጥ ሆኖ መለወጥ ከተቻለ አብሮ ለመስራት እና ህዝቡን በሙያ ለማገልገል ልብን ማስፋት አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ህሊናዬን ጠብቄ ከፖለቲከኛው ጋር አገልግላለሁ ካለ ምሁሩ በሙያው ህዝቡን ቢያገለግል አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ምሁር የሚስማማበትን ፖሊሲ እየደገፈ ስለማይስማማበት ፖሊሲ ድምፁን እያሰማ ህዝቡን በሙያው ለማገልገል ለአገር እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ መታገስ አለበት፡፡
ፖለቲከኛውም በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሰዎችን መሾሙን ትቶ ለሙያተኛው ምሁር ልቡን ቢያሰፋ ምሁሩም የሚነቅፈውም ፖሊሲ ቢኖርም ህዝቡን ግን በሙያው ለማገልገል ተጨማሪ ምእራፍ ቢሄድ አገር ታርፋለች፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍትህ #ፍርድ #ሙያ #እውቀት #ዲሞክራሲ #ታማኝነት #ፖለቲካ #አገር #እድገት #ድንበር #ኢትዮጲያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ምሁር #ፍቅር #ልብ #መሪ

No comments:

Post a Comment