Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, June 13, 2018

የህይወት ሚስጥር

ህይወት ሚስጥር ነው፡፡ ህይወትን የሰራውና የሰጠን እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ማስተዋሉ አይመረመርም፡
ህይወት በአንድ ቃል እንዲህ ነው ተብሎ አይተረጎምም፡፡
ከየት መጣሁ ወደየት እሄዳለሁ ለምን በዚህ ምድር ላይ አለሁ የሚሉት ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ማግኘት የህይወት ጥራታችንን ይወስነዋል፡፡ በዚህ ምድር የመኖር አላማዬ ምንድነው የሚለውን ማወቅ ይህንን የህይወት ስጦታ በደስታ ተቀብለን ለታለመለት አላማ እንድናውለው ያደርገናል፡፡   
የህይወትን ሚስጥር ማንም ፈላስፋ በትክክል ሊያስረዳን አይችልም፡፡ የህይወት ሚስጥር የምናገኘው የህይወትን ስጦታ ከሰጠን ከእግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
የህይወትን ሚስጥር የምንረዳው ህይወትን ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ህይወት ብዙ ብለዋል፡፡ ነገር ግን የህይወትን ሚስጥር በትክክል የምንረዳው ከመፅሃፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ስለህይወት እንዲህ ይላል፡፡
ሰው ህይወትን ለመረዳት ከፈለገ ኢየሱስን መረዳት አለበት፡፡ ካለ ኢየሱስ ህይወትን ለመረዳት መሞከር ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ የህይወት ትርጉም ኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ ህይወት ነው፡፡  
ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። የዮሐንስ ወንጌል 14፡6
ኢየሱስ የህይወት እንጀራ ነው፡፡ ሰው በህይወት አለመራብ ከፈለገ ኢየሱስን መገናኘት አለበት፡፡ ሰው በህይወት መርካት ከፈለገ ከኢየሱስ ጋረ መጣበቅ አለበት፡፡ ሰው ህይወትን መኖር ከፈለገ ኢየሱስን ማግኘት አለበት፡፡ ሰው ህይወትን መለማመድ ከፈለገ በኢየሱስ መኖርን መለማመድ አለበት፡፡  ሰው በህይወት መኖር ከፈለገ በኢየሱስ መኖር አለበት፡፡
ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። የዮሐንስ ወንጌል 6፡57
እውነተኛን ህይወት የምናጣጥመው በኢየሱስ ነው፡፡ እውነተኛን ህይወት ለማጣጣም ወደ ኢየሱስ መምጣት ግዴታ ነው፡፡
እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። የዮሐንስ ወንጌል 5፡39-40
እውነተኛ የህይወት ርካታ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስን በሚገባ በመከተል ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። የዮሐንስ ወንጌል 4፡13-14
ኢየሱስን ስንከተል የህይወትንም መንገድ እንከተላለን፡፡ ኢየሱስን ስናየው ህይወትን እናያለን፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36
በኢየሱስ ስንኖር በህይወት እንኖራለን፡፡ ከኢየሱስ ውጭ ስንኖር ከህይወት ውጭ እንኖራለን፡፡
በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡4-5
በኢየሱስ ስንኖር ለህይወት ሃይል እናገኛለን፡፡ በኢየሱስ ካልኖርን ለህይወት ሃይል አናገኝም፡፡ በኢየሱስ ካልኖርን በሃይል አንኖርም፡፡
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡5
የህይወት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #መደሰት #ስኬት #ህይወት #ስጦታ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #ማስተዳደር #እረፍት

No comments:

Post a Comment