Popular Posts

Friday, June 22, 2018

የትኛው ዲሞክራሲ?

ዲሞክራሲ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ዲሞክራሲ የሚደግፈንን ሰው መደገፍ ብቻ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ የሚቃወመንን መቀበል ነው፡፡ ዲሞክራሲ ከእኛ የተለየ ሃሳብ ያለውን ሰው ስፍራ መስጠት ማክበር ነው፡፡
ሰሞኑን ለዶክተር አቢይ ህዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቶዋል፡፡ ወደፊትን ድጋፉን ለመቀጠል ቁርጠኝነቱን በመግለፅ ላይ ይገኛል፡፡ መቼም ህዝብ የሚደግፈውና የህዝብን ልብ የሚያሳርፍ ሰው ማግኘት የእግዚአብሄር ስጦታ ነው እላለሁ፡፡
ግን ግን ሰው ሁሉ እንደዚህ ስሜታዊ በሆነበት ጊዜ አንድ ሰው ተነስቶ ዶክተር አቢይን አልደግፍም ቢል ምላሻችን ምን ይሆን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ መለስ ብለን ከስሜት ወጥተን መብቱ ነው ማለት እንችላለን ወይስ መሳደብ ማጥላላት ማንቋሸሽ መጥላት ይቀናናል?
መብቱ ነው ብለን ልባችንን ካሰፋን የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ገብቶናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አይ እንዴት ላይደግፍ ይችላል ችግር ስላለበት ብቻ ነው የማይደግፈው ካልን ግን ተሸውደናል፡፡ ዲሞክራሲ የምንለው ዲሞክራሲ ሳይሆን የምንቃወማቸው ሰዎች ሆኑ ብለን የምንለው አምባገነንነት ነው፡፡ መንግስትን የሚያስወቅሰው ነገር እኛ በማድረጋችን ትክክል አያደርገንም፡፡
ዶክተር አቢይን አብዛኛው ሰው የወደደበት ምክንያት ፍትሃዊ አመለካከት ስላንፀባረቀ ነው፡፡ የመንግስት ባልስላጣኖችንም ተቃዋሚዎችንም በእኩልነት በህገ መንግስቱ ስላያቸው ነው፡፡ ተቃዋሚ ህገ መንግስቱን ሲጥስ አሸባሪ መንግስት ግን ህገ መንግስቱ ሲጥስ ትክክለኛ አያደርገውም፡፡ ህገመንግስቱን መጣስ መንግስትም ያድርገው ተቃዋሚ አሸባሪነት ነው፡፡ ይህ መድልዎ የሌለበት የፍትህ አስተሳሰብ ነው፡፡
አሁንም እኛ ብዙ ስለሆንን ዶክተር አቢይን ስለደገፍን የማይደግፈንን ሰው ማስፈራራት እና ማንቋሸሽ ፍትሃዊ አያደርገንም፡፡
ሰብአዊ መብት ማንም ለማንም የማይሰጠው ከእግዚአብሄር የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ መንግስት ለህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቱን ያከብርለታል እንጂ ሰብአዊ መብት ማንም ለማንም በችሮታ የሚሰጥ ስጦታ አይደለም፡፡ ሰብአዊ መብት አብላጫ ድምፅ ያለው ለአናሳ ድምፅ ላለው በችሮታ የሚሰጠው መብት ሳይሆን ከእግዚአብሄር የተሰጠ ሰብአዊ መብት ነው፡፡
አንድ ሺህ ሰው ቢደግፈው የማይደግፈው አንድ ሰው የመቃወም መብቱ ሊከበር ይገባዋል፡፡ የዲሞክራሲ አንዱ መርህ አብላጫው ድምፅ ያለው ይመራል አናሳው መብቱ ይከበርለታል የሚል ነው፡፡ የራሱን ስሜት ብቻ የሚሰማ ሰው ለሌላው ድምፅ ቦታ የሌለው ሰው ከመንግስትም ስልጣን ይሁን በህዝብ መካከል በዲሞክራሲያዊ አገር ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ብዙም እንሁን ጥቂት በሃሳብ የማይመስለንን ሰው መጥላት ትክክል አያደርገንም፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ስንጠቀም የሌላውን ዲሞክራሲያዊ መብት በማክበር መሆን አለበት፡፡ ዲሞክራሲ የሁሉም ሰው አንድ አይነት መሆን ሳይሆን ከማይመስለን ሰው ጋር አብሮ የመኖርና በአንድነት ለአገር የመስራት የልብ ስፋት ነው፡፡
እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 4፡29
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍትህ #ፍርድ #አናሳ #አብላጫ #ዲሞክራሲ #ጭቆና #እምባገነን #ሰብአዊመብት #ድሃ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

No comments:

Post a Comment