Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, June 6, 2018

ከእርሱም ጋር እንዲኖሩ

ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ማርቆስ 3፡13-15
ኢየሱስ የጠራቸውን የጠራቸው በመጀመሪያ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ነው፡፡
ከእርሱ ጋር ያልኖርነውን ሰው አናውቀውም፡፡ ከእርሱ ጋር ያልኖርነውን ሰው አልሰማነውም፡፡ ከእርሱ ጋር ያለኖርነውን ሰው አላየነውም፡፡
አገልግሎት የቴክኒክ ጉዳይ አይደለም፡፡ አገልግሎት የሙያ ጉዳይ አይደለም፡፡ አገልግሎት የስራ ጉዳይ አይደለም፡፡
የቃሉ አገልግሎት መፅሃፍ ቅዱስን እንደ ሳይንስና ታሪክ አጥንተን የምናስተምረው ጉዳይ አይደለም፡፡
ክርስትና የግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ ክርስትና የህብረት ጉዳይ ነው፡፡ ክርስትና የማወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ክርስትና የማረፍ ጉዳይ ነው፡፡
ስላነበብነው ሳይሆን ስላወቅነው ጌታ ብቻ ነው ለሰዎች ማሳወቅ የምንችለው፡፡
ከራሱ የሰማነውን ጌታ ብቻ ነው ስለሰማነው ለሰዎች መናገር የምንችለው፡፡
ያገኘነውን ጌታ ነው ለሰዎች ማገናኘት የምንችለው፡፡ ከእሱ ጋረ በመኖር ያረፍነውን እረፍት ነው ለሌሎች የምናካፍለው፡፡ አብረነው የኖርነውን ሰው ብቻ ነው መንፈሱን የምንካፈለው፡፡
ክርስትና ያየነውን የምናሳይበት አገልግሎት ነው፡፡ ክርስትና የሰማነውን የምንናገርበት አገልግሎት ነው፡፡ ክርስትና የዳሰስነውን የምንመሰክርበት አገልግሎት ነው፡
ክርስትና የአሉ አሉ መልክተኝነት ሳይሆን ያየነውን የምንመሰከርበት አገልግሎት ነው፡፡
ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ 1ኛ ዮሐንስ 1፡1-2
የአገልግሎታችን መሰረቱ ከእርሱ ጋር መኖራችን ብቻ ነው፡፡
ከእርሱ ጋር በኖርንው መጠን እናገለግላለን፡፡ እርሱ በሰማነው መጠን ስለእርሱ መናገር እንችላለን፡፡ እርሱን ባየነው መጠን ስለእርሱ በትክክል ማሳየት እንችላለን፡፡ እርሱን በዳሰስነው መጠን ስለእርሱ ለሰዎች መናገር እንችላን፡፡
የአገልግሎታችን ዋናው ክፍል ከእርሱ ጋር መኖራችን ነው፡፡ ከእርሱ ጋር መኖራችን ለአገልግሎታችን መሰረት ነው፡፡ ከእርሱ ጋር መኖራችን የአገልግሎታችን ምንጭ ነው፡፡
በእርሱ መልክተኝነት የተገለገለ ሰው ብቻ ነው ተልኮ ማገልገል የሚችልው፡፡ የአገልግሎታችን ጉልበቱ ከእርሱ ጋር የመኖራችን ጉልበት ነው፡፡
ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21
ስለዚህ ነው አገልግሎት ከክርስቶስ ጋር የመገናኘት ከእርሱ ጋር የመኖር ጉዳይ እንጂ የቃላት ብልጫ አይደለም የሚባለው፡፡
እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡4-5
የፀሎት ጉልበታችን የሚመጣው በቃሉ አማካኝነት እርሱ ጋር በኖርነው መጠን ብቻ ነው፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ዮሃንስ 15፡7
ኢየሱስ አንድም ሰው ያላየውን እግዚአብሄርን ሊተርክ የቻለው ከእርሱ ጋር ስለነበረ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ስለ ክርስቶስ አንድም ነገር መተረክ የምንችለው ከእርሱ ጋር በኖርነው መጠን ብቻ ነው፡፡ የክርስትና ስልጣናችን የሚመጣው ብዙ የሚያባብል የጥበብ ቃል በማወቃችን መጠን ሳይሆን ስልጣን ካለው ጌታ ጋር በኖርነው መጠን ነው፡፡  
ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ማርቆስ 3፡13-15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #መኖር #ኑሮ #መላክ #ያየነውን #የሰማነውን #የዳሰስነውን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

No comments:

Post a Comment