Popular Posts

Wednesday, June 27, 2018

እግዚአብሔርን የሚያስክደን ክፉና የማያምን ልብ 8 ምልክቶች

ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ወደ ዕብራውያን 3፡12
አማኝ የነበረ ሰው ካልተጠነቀቀ በስተቀር አንድ ቀን ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክደው ክፉና የማያምን ልብ ሊኖረው ይችላል፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አመልካች ምልክቶች ሰው በአፉ ምንም ቢልም እንኳን ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክደው ክፉና የማያምን ልብ እንዳለው ያመለክታል፡፡
1.      በህይወታችን ለቁሳቁስ የመጀመሪያውን ስፍራ ስንሰጥ
ሰው እግዚአብሄርን ተስፋ ካላደረገ ተስፋ የሚሆነውን ነገር ይፈልጋል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ማመን ሲያቆም በቁሳቁስ ማመን ይጀምራል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ማመን ሲያቆም በገንዘብ ማመን ይጀምራል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር መገዛት ሲያቆም ለገንዘብ ይገዛል፡፡ ሰው ገንዘብን ሲወስድ እግዚአብሄርን ይጠላል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። የማቴዎስ ወንጌል 6፡24
2.     ስለዘላለም ህይወት ማሰብ ስናቆም
ሰው የሚያሳስበው የምድር ህይወት ብቻ ከሆነ ልቡ እግዚአብሄርን አስክዶታል ማለት ነው፡፡ ሰው በአፉ ምንም ቢናገር ነገር ግን ለዘላለም ህይወት አክብሮት ካጣ በእግዚአብሄር የፍርድ ወንበር ፊት እንደሚቀርብ ማሰብ ከተወ እግዚአብሄርን እንደካደ የሚያሳይ ጥሩ ምልክት ነው፡፡  
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡32
3.     ስለ እግዚአብሄር ፈቃድ ግድ ሳይኖረን ሲቀር
እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ምልክቱ ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው የመጀመሪያው ፍላጎቱ እግዚአብሄር በህይወቱ ያለውን አላማ ለመፈፀም የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈለግ ነው፡፡ ሰው ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈለግ ፍላጎቱን ካጣና ለእግዚአብሄር ፈቃድ ግድ ከሌለው እግዚአብሄርን እንደካደ አመልካች ነው፡፡
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 22፡42
4.     ለቤተክርስትያን የቤተሰብነት ስሜት ስናጣ
ሰው እግዚአብሄርን ሲያምን በምድር ላይ ያለው የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባል እንደሆነ የቤተሰብነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ ሰው ግን ለቤተክርስትያን የቤተሰብነት ስሜት ካጣ በቤተክርስትያን ላይ እንደፈለገ የሚናገርና የሚያደርግ ከሆነ እግዚአብሄርን እንደካደ አመልካች ነው፡፡
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡26-27
5.     ለእግዚአብሄር ቃል የነበረንን ክብደት ስናጣ
ሰው ለእግዚአብሄር ቃል ያለውን የመጀመሪያ ስፍራ ካጣ እና የእግዚአብሄርን ቃል እንደሰው ቃል ማየት ከጀመረ በአፉ ምንም ይበል ምን እግዚአብሄርን እየካደ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ሰው ሃሳቡን እንደ እግዚአብሄር ቃል መመዘኛ መመርመር ካቆመ እግዚአብሄርን እየካደ ነው፡፡
ስምዖን ጴጥሮስ፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ የዮሐንስ ወንጌል 6፡68
6.     እግዚአብሄርን መፍራት ስናቆም
ሰው እግዚአብሄርን መፍራት ካቆመና እግዚአብሄር እንደሚያይ እንደሚሰማና በሁላችን ላይ ዳኛ እንደሆነ ከረሳ እግዚአብሄርን  ክዶዋል፡፡ ሰው የዘራወን ያንኑ ደግሞ እንደሚያጭድ ካላወቀ እግዚአብሄርን የሚያስክድ ክፉ ልብ አለው ማለት ነው፡፡
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡7
7.     መፀለይ ስናቆም
እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው እግዚአብሄርን በመፈለግና በመፀለይ ይታወቃል፡፡ ሰው ግን መፀለይን ካቆመና ሁሉንም ነገር በራሱ ጉልበት ለመፍታት ከፈለገ እግዚአብሄርን የሚያስክድ ክፉና የማያምን ልብ እንዳለው ራሱን ይመርምር፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤የያዕቆብ መልእክት 4፡1-2
8.     እግዚአብሄርን መከተልና ማገልገል ከንቱ ነው ብለን ስናስንብ
ሰው በአፉ ላይናገረው ይችላል ነገር ግን እግዚአብሄርን ማገልገል ከንቱ ነው ብሎ ካሰበ እግዚአብሄርን የሚያስክድ ክፉና የማያምን ልብ እንዳለው አውቆ በንስሃ ይመለስ ፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የሚያስክድ #ክፉልብ #የማያምን #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment