Popular Posts

Monday, June 18, 2018

የእብዷ ተዋናይ ታሪክ

ግብዝነት ራስን አለመሆን ነው፡፡ ግብዝነት ያልሆኑትን መምሰል ነው፡፡ ግብዝነት ሌላውን ሰው ለመምሰል መሞከር ነው፡፡ ግብዝነት ራስን ያለመሆን አደገኛ እና አክሳሪ አካሄድ ነው፡፡   
የሆኑትን መሆን እንጂ ማስመሰል ከባድ ነው፡፡ ተፈጥሮን መሆን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ተፈጥሮን መሆን ይቀላል፡፡ ያልሆኑትምን መሆን ግን ይከብዳል፡፡ የሆኑትን መሆን የመሰለ ነፃነት የለም፡፡  
አንድ እብድ ድራማ የምትሰራ ሴት በቴሌቪዠን ቃለመጠይቅ ሲደረግላት ሰምቻለሁ፡፡ ድራማውን ስትሰራ እንደ እብድ ነው የምታስበው እንደ እንድ ነው የምትናገረው አኳኋኗ ሁሉ እንደ እብድ ነው፡፡ ታዲያ እንደእብድ ከምትሰራበትን ድራማ ስትጨርስ ወደ ጤነኝነት ሃሳብ ንግግርና አካሄድ ለመመለስ 2 ሰአት እንደ ሚፈጅባት በቃል መጠይቁ ላይ ስትናገር ሰምቻሉ፡፡
ይህች ሴት እንደ ጤነኛ ለመሆን ምንም ጥረት አይጠይቃትም፡፡ ጤነኛ ስለሆነች በቀላሉ እንደጤነኛ ታስባለች እንደጤነኛ ትናገራለች እንደጤነኛ ታደርጋለች፡፡ በቀላሉ ጤነኝነቱን ትኖረዋለች፡፡ ጤነኝነት ለእርስዋ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ጤነኝነት ለእርስዋ መኪናን እንደመንዳት ነው፡፡ እብደት ግን ለእርስዋ መኪናን እንደመግፋት ነው፡፡ እብደት ለእርስዋ ከተፈጥሮዋ ውጭ ስለሆነና በጤነኛ ሰው ስለሚሰራ ከባድ ነው፡፡
ጤነኛ ሳይሆኑ እንደጤነኛ መስራት ከባድ ነው፡፡ እብድ ሳይሆኑ እንደ እብድ ድራማ መስራት ከባድ ነገር ነው፡፡ ያልሆኑትን መሆን እጅግ ከባድ ነው፡፡
እንዲሁ ማስመሰልና ግብዝነት ከባድ ነገር ነው፡፡ ግብዝነት ህይወትን ያሳሰባል፡፡ ግብዝነት ጉልበትን በከንቱ ያባክናል፡፡
ግብዝነት የሆኑትን ካለመቀበል ይመጣል፡፡ ሰው ራሱን ካልተቀበለ እጅግ በጣም ችግር ነው፡፡ ሰው በራሱ ካልተማመነ ከባድ ነው፡፡ ሰው ባለከው ደረጃ ካልረካ ችግር ነው፡፡ ሰው ባለው ነገር ካፈረ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ሰው በደረሰበት ደረጃ ካልረካ ትልቅ ችግር ነው፡፡
ሰው ራሱን ካላደነቀ ሰው ራሱን ካልሆነ የችግሮች ሁሉ መንስኤ ይሆናል፡፡ ሰው ለራሱ አክብሮት ከሌለው እና ሌላውን መምስል ከፈለገ ውድቀት ነው፡፡
ሰው ለውስጥ ህይወቱ ቅድሚያ ካልሰጠና ለውጭ ህይወቱ እጅግ ከተጨነቀ ችግር ነው፡፡ ሰው ለችግሩ ምንጭ መፍትሄ ካልሰጠ ለሚታየው የችግሩ ውጤት ከተጨነቀ መፍትሄ ያለው ህይወት መኖር ያቅተዋል፡፡
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። የማቴዎስ ወንጌል 23፡25-27
ግብዝነት እግዚአብሄር የሚያየው ልብን ሳይሆን ፊትን ነው ብሎ መሳሳት ነው፡፡
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7
ግብዝነት ከሰው የሚገኘውን ክብር እንጂ ከእግዚአብሄር የሚገኘውን ክብር አለመፈለግ ነው፡፡
ከሰው ክብርን አልቀበልም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? የዮሐንስ ወንጌል 5፡4141-42፣44
ግብዝነት ውስጥን ላለማጥራት መስነፍ ነው፡፡ ግብዝነት ውስጥን በትጋት ያለማጥራት ስንፍናና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ራስን አለመስጠት ነው፡፡ ግብዝነት ራሰን ለማንፃት ከመትጋት ይልቅ በውጭው በመጣፍና በመሸፋፈን ሰውን ለመሸወድ መሞከር ነው፡፡
ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል፡፡ እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። የሉቃስ ወንጌል 11፡39-41
ግብዝነት ለውስጥ ውበት ሳይሆን ለውጭ ውበት ይበልጥ ዋጋ መስጠት ነው፡፡ ግብዝነት ዋጋ ያለውን ነገር አለማወቅ ዋጋው ላነሰ ርካሽ ነገር ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1 የጴጥሮስ መልእክት 3፡3-4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ ##ግብዝ #ውጭውን #ውስጡን #ልብ #ውበት #ዋጋ #ፊት #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment