Popular Posts

Wednesday, June 27, 2018

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና

አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። መዝሙረ ዳዊት 139፡13-16
እግዚአብሄርን ከማወቅ ቀጥሎ ራስን ማወቅ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄርን አውቀን በመልኩና በአምሳሉ የሰራንን ራሳችንን ካላወቅን በእርሱና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት ሊሳካ አይችልም፡፡ ራሳችንን ካላወቅን ከእግዚአብሄር ጋርና ከሌላው ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡
በመድር ላይ ያሉ አብዛኛው ችግሮች መንስኤ የሰው እግዚአብሄርን ያለማወቅና ራስን ያለማወቅ ችግር ነው፡፡
ሰው ራሱን ካላወቀና እግዚአብሄር እንደሚያየው አድርጎ ካላየ ከእግዚአብሄር ጋርም ከሰውም ጋርም እንዴት እንደሚኖር ማወቅ አይችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄር እንደሚያየው ራሱን ካላየ እግዚአብሄር በህይወቱ ያለውን አላማ ለመፈፀም አይችልም፡፡
እግዚአብሄር ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር በመድር ላየ እንድንሰራ ለፈለገው ነገር በቂ ነገር በእኛ ውስጥ ፈጥሮአል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ሊፈፅም ላሰበው ነገር የሚጎድለን ምንም እምቅ ሃይል የለም፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3
ሰይጣንም በመጀመሪያ የሰው ልጅን የተዋጋው ሰው ያለውን ማንነት በማበላሸትና ለራሱ ያለውን መረዳት በማሳሳት ነው፡፡
እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡4-5
አሁንም ሰይጣን የሚጎድልህ ነገር አለ ፣ እግዚአብሄር የደበቀህ ነገር አለ ወይም እግዚአብሄር ከሚያስፈልግህ ነገር አጉድሎብሃል ብሎ በውሸት ካሳመነህ ትወድቃለህ፡፡ 
ነገር ግን ውብና ድንቅ አድርጎ ሰርቶኛል፡፡ እኔ የእርሱ የፈጠራ ውጤት ማሳያ ነኝ፡፡ እኔ የእግዚአብሄር የእጅ ስራ ነኝ፡፡ እኔ በህይወት ያለኝን አላማ ለመፈፀም ፍፁም ተደርጌ ተፈጥሬያለሁ ካልክ ታሸንፋለህ፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡10
እግዚአብሄር ውብና ድንቅ አድርጎ እንደሰራኝ ራሴን ከተቀበልኩ አሸንፋለሁ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የፈጠረኝ አፈጣጠር ላይ የማወጣው አቃቂር ካለ የህይወት አላዬን መፈፀም ያቅተኛል እሸነፋለሁም፡፡
ራሱን ያልተቀበለ ሰው ሌላውን ሊቀበል አይችልም፡፡ ሌላውን ያለመቀበል ችግር ወደኋላ ቢጠና ራስን ያለመቀበል ችግር መንስአኤ ነው፡፡
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙረ ዳዊት 139፡14
ምንም ሳላሻሽልና ሳልቀንስ ሳልጨምር ራሴን እቀበለዋለሁ፡፡ ማንም በፍጥረቴ ላይ ጥያቄ ቢኖረው ምንም ማድረግ አልችልም አዝናለሁ፡፡ እኔ ግን ፍጥረቴን እወደዋለሁ፡፡ እኔ ግን በፍጥረቴ ላይ ምንም የማወጣው እንከን የለም፡፡
እግዚአብሄር የፈጠረው የቆዳዬ ቀለም ፣ ቁመቴ ፣ ዘሬ ፣ መልኬ ፣ አስተዳደጌና ባህሪዬ ምንም አይወጣለትም፡፡ ስለ ቆዳዬ ቀለም ፣ ስለ ቁመቴ ፣ ስለ ዘሬ ፣ ስለ መልኬ ፣ ስለ አስተዳደጌና ስለ ባህሪዬ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም፡፡ ማንም በአፈጣጠሬ ላይ እንከን ያገኘበት ካለ ንስሃ ይግባና ይመለስ፡፡ ማንም ሰው አይኑ ተለቅ ቢል ኖሮ ጥሩ ነበር ቢል ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን የእጅ ስራ የማስተካክል እኔ ማነ ነኝ?
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ግሩም #ድንቅ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ከፍታ

No comments:

Post a Comment