Popular Posts

Follow by Email

Thursday, June 14, 2018

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካበት 12 መፅሃፍ ቅዱሳዊ መለኪያዎች

መጋቢነት ለሰዎች ነፍስ የመትጋት የተከበረ ጥሪ ነው፡፡
ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።፡ወደ ዕብራውያን 13፡7
መጋቢነት በእግዚአብሄር የሚሰጥ ፀጋ እንጂ በሰው አነሳሽነትና ፍላጎት የሚደረግ አገልግሎት አይደለም፡፡ ማንም ሰው ማንንም ስው ለመጋቢነት ሊጠራ አይችልም፡፡ ሰውም ራሱን ለመጋቢነት ሊያሰማራ አይችልም፡፡ የመጋቢነትን ፀጋ ሰጥቶ ሰውን ለመጋቢነት የአገልግሎት ስራ ሊጠራ የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡11
ሰው በአካባቢው ያለውን ክፍተት አይቶ መጋቢ መሆን አይችልም፡፡ ሰው ስለፈለገና ስለተመኘ ብቻ መጋቢ መሆን አይችልም፡፡ ሰው የሚመገቡ ሰዎች ስላሳዘኑት ብቻ መጋቢ ሊሆን አይችልም፡፡ መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ጥሪ ነው፡፡ መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ የአገልገሎት ስጦታ ነው፡፡ መጋቢነት ፀጋ ነው፡፡
መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ስጦታ ስለሆነ ብቻ ታማኝነቱ አይለካም ማለት አይደለም፡፡ ሰው በመጋቢነት ተጠርቶ ታማኝ ሊሆን ይችላል ታማኝ ላይሆን ይችላል፡፡ በመጋቢነት የተጠራ ሰው ታማኝ መሆን እግዚአብሄርም የእግዚአብሄርም ህዝብ ይጠብቅበታል፡፡  መጋቢነት በእግዚአብሄር ቃል ይመዘናል፡፡ 
የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካባቸው መንገዶች አሉ፡፡ እንዲሁም የመጋቢ ታማኝነት የማይለካባቸው መንገዶች አሉ፡፡
1.      መጋቢነት በሰው ብዛት አይለካም
ብዙ ሰው የሚመግብ ሰው የተሳካለት ትንሽ ሰው የሚመግብ ሰው ያልተሳካለት አይደለም፡፡ የሰው መጋቢነት የሚለካው እግዚአብሄር እንዲመግብ በሰጠው ሰዎች ላይ ባለው አገልግሎት ነው፡፡ የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ራሳቸውን የሰጡትን ሰዎች የእግዚአብሄር ቃል በታማኝነትና በትጋት በመመገቡ ነው፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው የተሰጠውን ሰዎች እንዴት በትጋት እንዳገለገላቸው በተሰጠው ሰው ብቻ ነው፡፡  
እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን። እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡1-2
2.     የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን በማሳደግ አይደለም፡፡  
የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የላከለትን ሰዎች ኮትኩቶ ለማሳደግ ባለው ትጋት ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ባሳደገው ሰው ቁጥር አይደለም፡፡ የመጋቢው ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን በማሳደግ አይደለም፡፡ ሰዎች ለማደግ የሚያሳድገውን የእግዚአብሄርን ቃል የሚያስተራቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም ለማደግና ለመለወጥ የሚያደርጉት እርምጃ ያሳድጋቸዋል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው በማሳደግ ሳይሆን የሚያሳድገውን የእግዚአብሄርን ቃል በትጋት እና በታማኝነት በማቅረብ ነው፡፡
እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡6-8
3.     የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠውን ሰዎች በእግዚአብሄር ቃል አውቀት ከመንፈሳዊ ከድካምና ከበሽታ ከሞት እንዲጠበቁ የሚያስችላቸውን ትምህርት ፣ ምክርና እንክብካቤ በማድረጉ ነው፡፡ የመጋቢ ሃላፊት መወጣቱ የሚመዘነው ንፁሁን የእግዚአብሄርን ቃል በተመጣጠነ ሁኔታና በሚዛናዊነት በመመገብ ራሳቸውን ከስህተት እንዲከላከሉ በማስታጠቅ ነው፡፡
ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም። ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። የሐዋርያት ሥራ 20፡20-21፣26-27
4.     የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ምእመኑን በመጎብኘቱ ነው፡፡
መጋቢ የእግዚአብሄርን ህዝብ ከላይ ሆኖ ሊከታተል ይገባዋል፡፡ መጋቢ የእግዚአብሄር ህዝብ መንፈሳዊ ህይወት የበላይ ጠባቂ ነው፡፡ መጋቢ ከላይ ሆኖ መንጋውን ከተኩላ የሚጠብቅና የሚከላከል ጠባቂ ነው፡፡
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።  የሐዋርያት ሥራ 20፡28-30
5.     የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የእግዚአብሄርን ቃል ምሳሌ በመሆን ነው፡፡
የመጋቢ ታማኝዕነት የሚለካው የሰዎችን ህይወት በመለወጥ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ቃል በአስተሳሰብ ፣ በንግግርና በአካሄድ ሞዴል ወይም ምሳሌ በመሆን ነው፡፡
ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1 የጴጥሮስ መልእክት 5፡3
የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ወደ ዕብራውያን 13፡7
6.     የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ለህዝቡ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ነው ነው፡፡
የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን ከልሎ አስቸጋሪ ሁኔታን በመጋፈጡ ነው፡፡ ጠላት ህብረትን መበተን ሲፈልግ የሚመታው በስፍራው ያለን መሪ ነው፡፡ እረኛን ከመታ በጎች እንደሚበተኑ ያውቃል፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው ህዝቡን ይዞ በታማኝነት መዝለቁ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲመጣ ህዝቡን ጥሎ የሚሸሽ መጋቢ ታማኝ መጋቢ አይደለም፡፡
እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።  የዮሐንስ ወንጌል 10፡12-13
7.     መጋቢ ታማኝነት የሚለካው መጥፎ ጥቅምን ባለመመኘት ነው
የመጋነት ታማኝነት የሚለካው ያለኝ ይበቃኛል በሚል አስተሳብን ነው፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6፣8
የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን ለጥቅማቸው እንጂ ለጥቅሙ ባለመፈለግ ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው በበጎ ፈቃድ በማገልገል ፣ በመስጠትና በመጥቀም ነው፡፡ የመጋቢ ማማኝነት የሚለካው ምእመኑን በክርስቶስ ደም እንደተገዛ ክቡር የእግዚአብሄር ህዝብ እንጂ እንደ ጥቅም ማግኛ ምንጭ ባለመመልከት ነው፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው ህዝቡን እንዲያገለግል የጠራውን እግዚአብሄርን እንጂ ህዝቡን እንደ ገቢ ምንጭ ባለማየት ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅ ሲፈልግ እግዚአብሄር የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚጨምርለት በማመን ነው፡፡
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡32-33
የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ያለኝ ይበቃኛል በማለቱ ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠውን ተሰሚነት ተጠቅሞ የህዝቡን መብዛት እንጂ የራሱን መብዛት ባለመፈለግ ነው፡፡
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3
እነሆኝ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 12፡3
8.     የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን መታገስ በመቻሉ ነው
መሪነት ወደሰው ደረጃ ወርዶ ሰውን ታግሶና ተሸክሞ ወደሌላ ደረጃ የማድረስ ጥበብ ነው፡፡ መጋቢነት ህዝቡን እግዚአብሄር ወደአየላቸው ደረጃ ለማድረስ በትግስትና በትጋት ማገልገል ነው፡፡  
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡1-2
እርሱም አለው፦ ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ። ኦሪት ዘፍጥረት 33፡13
9.     የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡ እግዚአብሄር ወዳየላቸው ቦታ መምራቱ ነው፡፡
የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ስለ ህዝቡ ከእግዚአብሄር ራእይን በመቀበል ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን እግዚአብሄር ወደ አየላቸው ቦታ መውሰዱ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ወደአየላቸው ቦታ መድረስ የመጋቢውም የተመሪውን ሃላፊነት ነው፡፡ መጋቢው ስለፈለገ ብቻ ህዝቡን እግዚአብሄር ወደአየላቸው ቦታ መውሰድ አይችልም፡፡ የህዝቡ መሰጠትም ይጠይቃል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር ለህዝቡ በልቡ ያለውን መፈለግና ህዝቡን እግዚአብሄር  ወደአየላቸው ደረጃ መምራት ነው፡፡ ህዝቡ ታማኝ ሆኖ ከተከለተለ እግዚአብሄር ወደአየለት ቦታ ይፈደርሳል፡፡
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡28-29
10.    የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን ለአገልዕግሎት ስራ በማስታጠቅና በማሰማራት ነው
መጋቢ እርሱ ብቻ ጠቃሚ ሌላው ሰው ሁሉ ተጠቃሚ ማድረግ የለበትም፡፡ እርሱ ካህን ሌሎች ህዝብ መሆን የለባቸውም፡፡ እርሱ ጠቃሚ ሌሎቹ ሁሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም፡፡ መጋቢ ህዝቡን ሁሉ ሰራተኛ የሚያደርግ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡12-13
ግልገሎቼን አሰማራ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ። የዮሐንስ ወንጌል 21፡15፣17
11.     መጋቢ የበደለን በመገሰፅ የቤተክርስትያንን ቅድስና በመጠበቅ ታማኝነቱ ይታያል፡፡
መጋቢ እግዚአብሄርን ሳይሆን ሰውን ሊያስደስት የሚጥር ከሆነ ለጥሪው ታማኝ አይሆንም፡፡ መጋቢ የማስደስተውን ሰውን ስለስህተቱ መገሰፅ መማር አለበት፡፡ መጋቢ ሰውን የመገሰፅ ደስ የማያሰኝ ሃላፊነት በትጋት መወጣት አለበት፡፡ መጋቢ ለቤተክርስትያን ንፅህናና አንድነት ሰዎችን የማረምና የመቅጣት የቤተክርስትያን አባትነት ታማኝነቱን በትጋት መወጣት አለበት፡፡  
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡28-29
ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡12-13
12.    መጋቢ እግዚአብሄርን በመውደድ የእግዚአብሄርን ህዝብ በመውደድና በመማር ታማኝነቱ ይለካል፡፡
መጋቢ የማይራራለትንና የማይወደውን ህዝብ ማገልገል አይችልም፡፡ መጋቢ የእግዚአብሄርን ህዝብ ሲያገለግል ብዙ ነገሮች መጣል ይገጥመዋል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የበደለውን ሰው ይቅር በማለትና ባለመጥላት ነው፡፡
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡1-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ጥሪ #መገሰፅ #መምራት #ማሰማራት #መታገስ #መመገብ #መኮትኮት #ማሰማራት #መጠበቅ #ምሳሌ #ፍቅር #ምህረት #ይቅርታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

No comments:

Post a Comment