Popular Posts

Follow by Email

Monday, June 4, 2018

ተዘዋዋሪ የሰይጣን አምልኮ

ሰይጣን ከመውደቁ በፊት የእግዚአብሄር አገልጋይ ነበር፡፡ ሰይጣን የወደቀው በእግዚአብሄር ላይ በማመፁ ነው፡፡ ሰይጣን የወደቀው እንደ እግዚአብሄር ለመመለክ በመፈልግ ምኞት ነው፡፡ ሰይጣን መመለክ ይፈልጋል፡፡ 
ሰይጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መመለክን ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን ኢየሱስን በግልፅ ብታመልከኝ ይህን ክብር ሁሉ አሰጥሃለሁ ብሎታል፡፡
ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ሉቃስ 4፡5-7
ሰው ካመለከው እና ከተንበረከከለት ሰይጣን በየደረጃው የአለምን ክብር ለሰው ለመስጠት ዝግጁ ነው፡፡
አሁን ሰይጣን የሚመለከው እንደ ኢየሱስ በግልፅ ጠይቆ ላይሆን ይችላል፡፡ በግልፅም ይሁን በስውር ሰይጣን መመለክን ይፈልጋል፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሰይጣን መመለክን ይጠይቃል፡፡
የሰይጣን አምልኮ በጣም በታዋቂ ሰዎች ላይ ብቻ ያለ የሚመስላቸው ሰዎች ተሳስተዋል፡፡ ሰይጣን የእግዚአብሄር መልክና አምሳል ያለበትን ማንንም አይንቅም፡፡ ሰይጣን የእግዚአብሄር መልክና አምሳል ያለበትን ሰው ማስመለክ እግዚአብሄርን ራሱን ያገኘውና ያሸነፈው ይመሰለዋል፡፡
ሰይጣን ከማንም ሰው አምልኮን ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ከተፈጠር ከማንም ሰው የሚመጣውን አምልኮ አይንቅም፡፡ ሰይጣን አንዳንድ ጊዜም ቢሆን የመስረቅ የማረድ የማጥፋት አላማውን የሚያሳካለትን ሰው ይፈልጋል፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ ዮሃንስ 10፡10
ሰይጣን ለማምለክ የሰይጣን ጉባኤ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ሰይጣንን ለማምለክ የሰይጣን ስብሰባ አባል መሆንም አይጠይቅም፡፡ ሰይጣንን እምቢ ለማለት እግዚአብሄርን እምቢ ማለት ብቻ ይበቃል፡፡ ሰይጣንን ለመታዘን እግዚአብሄርን አለመታዘዝ ብቻ ይበቃል፡፡ ሰይጣንን ለመከተል በውሸት መመላለስና የሰይጣንን ምኞት ጥላቻንና ነፍሰ ገዳይነትን ማድረግ በቂ ነው፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሃንስ 8፡44
ሰይጣንም ለማምለክ ሰይጣንን የሚያስደስተውንና ሰይጣን የሚበላውን ነገር ሃጢያትን መለማመድ ይበቃል፡፡ ሰይጣንን ለማምለክ እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ነገር ማድረግ ይበቃል፡፡ ሰይጣንን ለማምለክ የእርሱን ጥበብ መከተል በቂ ነው፡፡
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡14-16
ሰይጣንን ለማምለክ ብልቶቻችንን የፅድቅ የጦር እቃ አድርጎ ለእግዚአብሄር አለማቅረብ ይበቃል፡፡ የሰይጣንን ስራ ለመስራት ብልቶችን የአመፅ የጦር እቃ አድርጎ ለሃጢያት ማቅረብ በቂ ነው፡፡
ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ሮሜ 6፡13
በሰይጣን አምልኮ ስር ለመውደቅ ጌታን ሳይሆን ራስን በህይወታችን ላይ ጌታ ማድረግና ማንገስ ይበቃል፡፡ ሰው ጌታ ጌታው ካልሆነ ከመቀፅበት ሰይጣን ጌታው ይሆናል፡፡ ሰው የጌታን ፈቃድ ካልሰማ የሰይጣንን ፈቃድ ይሰማል፡፡ ሰው ጌታን ሳይሆን ራሱን በላዩ ላይ ከሾመና ጌታ ካደረገ በሰይጣን ጌትነት ስር ይወድቃል፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2
በሰይጣን ለመዋጥ በእግዚአብሄር ነገር ንቁ አለመሆንና በመጠኑ አለመኖር በቂ ነው፡፡
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8
በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ለመውደቅ የባለጠግነት መኞትን መከተል በቂ ነው፡፡
ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡9-10
ከሳይጣን ጋር ለማበር እና ሰይጣንን ለማምለክ የእግዚአብሄርን ስራ መቃወም በቂ ነው፡፡ ሰይጣንን ለማምለክ የእግዚአብሄር ስራ ላይ መነሳት በቂ ነው፡፡ በሰይጣን ወጥመድ ለመያዝ በአመፅ መቀጠልና ንስሃ አለመግባት በቂ ነው፡፡
ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡25-26
በሰይጣን ሃሳብ ውስጥ ለመውደቅ መራርነትና ይቅር አለማለት በቂ ነው፡፡ በህይወታችን ለሰይጣን ስፍራ መስጠት በምህረት አለመመላለስ በቂ ነው፡፡   
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን ሰዎች 4፡27
የሰይጣንን ፈቃድ ለማድረግ የልቦናችንን ፈቃድ ማድረግ በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ካላደረግን የስጋችንን ፈቃድ በማድረግ በተዘዋዋሪ የምናደርገው የሰይጣንን ፈቃድ ነው፡፡
በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌሶን 2፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #የስጋፈቃድ #የልቦናፈቃድ #ምኞት #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አምልኮ #እምነት #ነፃነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment