Popular Posts

Saturday, June 16, 2018

እንደልቤ የተባለው ዳዊት 7 የልብ ውበቶች

ዳዊት እግዚአብሄር እንደልቤ ያለው ሰው ነው፡፡
እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ። የሐዋርያት ሥራ 13፡22
ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ ተብሎ የተመሰከረለት የተባረከ ሰው ነው፡፡
ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤የሐዋርያት ሥራ 13፡36
የዳዊትን የልብ ባህሪያት ማጥናት እኛም በዘመናችን የእግዚአብሄርን ልብ ተረድተን የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግለን እንድናልፍ ያስታጥቀናል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1 የጴጥሮስ መልእክት 3፡4
1.      ዳዊት የምስጋናን መስዋእት ያቀርባል
ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው ሲመቸው ብቻ አይደለም፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው የሚፈልገው ነገር ሁሉ እንደተሟላለት ካረጋገጠ በኋላ አይደለም፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው ሁልጊዜ ነው፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው በችግር ጊዜም ነው፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው ማጉረምረም በሚያምረው ጊዜ ነው፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚያመሰግነው ከማመስገን ይልቅ ማጉረምረም በሚቀልበት ጊዜ ነው፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚየመሰግነው ለማጉረምረም ብዙ ምክኒያቶች እያሉ ነው፡፡
ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ መዝሙረ ዳዊት 50፡14
ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። መዝሙረ ዳዊት 42፡11
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18
2.     ዳዊት ለእግዚአብሄር ስርአት አክብሮት አለው
ዳዊት የመርህ ሰው ነው፡፡ ዳዊት ስሜታዊ ሰው አይደለም፡፡ ዳት የእግዚአብሄን ስርአት ያውቃል ያከብራል፡፡ ዳዊት የእግዚአብሄርን ስርአት ለመጠበቅ ይጠነቀቃል፡፡ ዳዊት ሳኦል በሚያሳድደው ጊዜ ሊገድለው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር በተቀባው ላይ እጄን አላነሳም አለ፡፡
ሰዎቹንም፦ እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 24፡6
ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡1-2
3.     ዳዊት ሲሳሳት ለንስሃ ፈጣን ነው
ዳዊት ጥማቱና ረሃቡ በእግዚአብሄር ፊት ትክክል ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ዳዊት ሲሳሳት ይመለሳል፡፡ ዳዊት ሲሳሳት ራሱን ያዋርዳል፡፡ ዳዊት ከሃጢያቱ በፍጥነት ይመለስም ነበር፡፡ ዳዊት በእግዚአብሄርን በሰውም ፊት ለመዋረድ ዝግጁ ነበር፡፡
ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። መዝሙረ ዳዊት 51፡2-5
4.     ዳዊት ለሰው ፍቅር አለው
ዳዊት ለሰው ፍቅር እና አክብሮት አለው፡፡ ዳዊት ሰዎችን በማገልገል ይረካል፡፡ ዳዊት በሰዎች በመጠቀም ላይ አያተኩርም፡፡ ዳዊትን የተከተሉት ሰዎች የተጨነቁ ብድር ያለባቸው እና የተከፉ ሰዎች ነበሩ፡፡
የተጨነቀውም ሁሉ፥ ብድርም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተከማቸ፤ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 22፡2
ዳዊት እነርሱን በመምራትና በማገልገል ሃያላን አደረጋቸው፡፡ /መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ 23፡8-39/
ዳዊት አንድ ጊዜ የሚጠጣው ውሃ በፈለገ ጊዜ ሃያላኑ በህይወታቸው ተወራርደው የፍልስጤምን ሰራዊት ሰንጥቀው የሚጠጣውን ውሃ አመጡለት፡፡ እርሱ ግን ለእነዚያ ሰዎች ከነበረው ክብር አንጻር በመሬት ላይ ደገፋው፡፡
ዳዊትም፦ በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ። ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ፦ አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ 23፡15-17
5.     ዳዊት ለቃሉ የመጀመሪያውንም ስፍራ ይሰጣል
ዳዊት በክፋት ላለመሄድ ይጠነቀቃል፡፡ ዳዊት እግዚአብሄርን እንዳይበድል የእግዚአብሄርን ቃል በልቡ ይሰውራል፡፡
ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
መዝሙረ ዳዊት 1፡1-3
አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። መዝሙረ ዳዊት 119፡11-12
ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። መዝሙረ ዳዊት 119፡127
6.     ዳዊት የእግዚአብሄርን ቤት ይወዳል
ዳዊት የእግዚአብሄርን ቤት ይወዳል፡፡ ዳዊት ለእግዚአብሄር ቤት የማያደርገው ነገር የለም፡፡ ዳዊት የእግዚአብሄርን ቤት ለማገልገል ቀን ከሌሊት በትጋት ይሰራል፡፡
አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። መዝሙረ ዳዊት 132፡1-6
7.     ዳዊት የእግዚአብሄርን ምሪት ያስቀድማል፡፡
ዳዊት እግዚአብሄር እንዳለበት ያላረጋገጠውን ነገር ላለማድርግ ይጠነቀቃል፡ሸ ዳዊት በራሱ ማስተዋል አየደገፍም፡፡ ዳት በመንገዱ ሁሉ ለእግዚአብሄር ምሪት እውቅና ይሰጣል፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። ምሳሌ መጽሐፈ ምሳሌ 3፡5-6
ዳዊት ጠላቶች መጥተው በዘረፉት ጊዜ እንኳን ለምንም ነገር አይቸኩልም ነገር ግን ልውጣባቸውን አሳልፈህ ትሰጠኛለህን ብሎ የእግዚአብሄርን ምሪት ይጠይቃል፡፡  
ዳዊትም፦ የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም፦ ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 30፡8
ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። ዳዊትም፦ ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን፦ ፍልስጥኤማውያንን በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ 5፡18-19
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፀጋ #ምህረት #ቃል #መባረክ #አገልግሎት #መዋረድ #ምስጋና #ምሪት #ፀጋ #ንስሃ #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #ዳዊት #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ልብ #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment