Popular Posts

Tuesday, June 19, 2018

ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም

አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ትንቢተ ሐጌ 1፡5-7
በህይወት የምንሰራቸው ነገሮች ውጤት አምጥተዋል ማለት ትክክል ነን ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በሰው ውስጥ ያስቀመጠው እምቅ ጉልበት አለ፡፡ ያንን እምቅ ጉልበት ከተጠቀመ ሰው ውጤታማ ይሆናል፡፡ ሰው የሚፈልገውን ነገር አገኘ ማለት ግን በእግዚአብሄር ዘንድ ስኬታማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሰው የሚፈልገውን ነገር አገኘ ማለት በእግዚአብሄር አይን ውጤታማ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
አንዳንድ እግዚአብሄርን ሳንሰማ በራሳችን አነሳሽነት የምናደርጋቸው ነገሮች ብክነታቸው ይበዛል፡፡ አንዳንድ እግዚአብሄርን ሳንጠብቅ የምናደርጋቸው ነገሮች በህይወት ለብዙ አዳ ያጋልጡናል፡፡  
እውነት ነው ምንም ብንሰራ ጥቅም እናገኛል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን ሳንጠብቅ የምናደርጋቸው ነገሮች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ እግዚአብሄርን ሳንሰማ በራሳችን አነሳሽነት የምናደርጋቸው ነገሮችን እግዚአብሄር ሃላፊነትን አይወስድም፡፡
ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። ትንቢተ ሐጌ 1፡6
ስለዚህ ነው በፍቅር የማይደረግ ነገር ምንም እንደማይጠቅም መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡  
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡2-3
በእግዚአብሄር ሃሳብ የማይሰበሰብ ሰው ምንም ቢሰበስብ እንደማይጠቀም መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡15
ሰው በከንቱ ይጓጓል እንጂ ያለ እግዚአብሄር ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማንም የለም፡፡ እግዚአብሄርን ሳንሰማ የምናደርገው ነገር ወጭውና ገቢው አይመጣጠንም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳንከተል የምናደርገው ነገር ወጭው ብዙ ገቢው ግን ጥቂት ይሆናል፡፡ እግዚአብሄርን ሳንሰማ የማደርገው በነገር ቁሳቁስ ሊያስገኝልን ይችላል እርካታ ፣ ሰላምና ደስታ ግን አይሰጠንም፡፡ እግዚአብሄርን ሳንታዘዝ የምናደርገው ነገር በሰው ዘንድ ሊያስመሰግነን ይችላል እግዚአብሄርን ግን አናታልለውም፡፡   
ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማነው? መጽሐፈ መክብብ 2፡25
እግዚአብሄር የሰራውን አብረህ ስትሰራ ብቻ ነው ትርፋማ የምትሆነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ካልሰራ ሰራተኛ በከንቱ ይደክማል፡፡ እግዚአብሄር የጠበቀውን አብረህ ስትጠብቅ ነው ፍሬያማ የምትሆነው ካለበለዚያ ግን መትጋትህ አይቀርም ግን በከንቱ ትተጋለህ፡፡
እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ። መዝሙረ ዳዊት 127፡1-2
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #መዳን #እምነት #ማስተዋል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ማሰብ #መሪ

No comments:

Post a Comment