Popular Posts

Tuesday, June 5, 2018

ሕያው ሆኜ አልኖርም

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
ኢየሱስ የሞተው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሞተልን እኛ ለእርሱ ልንሞት ይገባናል፡፡ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ለፍላጎቱ ለምርጫው እና ለምቾቱ እንደሞተ ሁሉ እኛም ለፍላጎታችን ለምርጫችንና ለምቾታችን መሞት ይገባናል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ እኛ የምንፈልገውን እንጂ እሱ የሚፈልገውን አላደረገም፡፡ እኛም ክርስቶስ የሚፈልገውን እንጂ እኛ የምንፈልገው ማድርግ የለብንም፡፡ ክርስቶስ ለእኛ የሚመርጠውን እንጂ እኛ ለራሳችን የምንመርጠውን እንድናደርግ አይገባም፡፡ እርሱ የሚያምረውን እንጂ ራሳችን የሚያምረንን እንድናደርግ አልሞተልንም፡፡
ለራሳችን ፍላጎት ሞተን ለእርሱ ፍላጎት ህያው እንድንሆን ሞቶልናል፡፡ የራሳችንን ምርጫ ወደጎን አድርገን የእርሱን ምርጫ እንድንከተል ራሱን አሳልፎ ሰጥቶዋል፡፡ ለራሳችን ሞተን ለእርሱ ህያው እንድንሆን ስለፈለግ ስለእኛ ሞተ፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። ሉቃስ 17፡33
ለራሳችን ፍላጎትና ምርጫ ሞተን ለእርሱ ፍላጎትና ምርጫ ለመኖር በምድር ላይ አለን፡፡ ኢየሱስን የሚከተል ሰው ሆኖ ለራሱ ጥቅም የሚኖር የለም ለራሱ ጥቅም የሚሞት ሰው የለም፡፡ የምንኖረው ለክርስቶስ ኢየሱስ ነው የምንሞተው ለክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡   
ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ሮሜ 14፡7-8
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው እኔ ህያው ሆኜ አልኖርም የሚለው፡፡ ሃዋሪያው ጳውሎስ ክርስቶስ የሚፈልገውን ያደርጋል ክርስቶስ የማይፈልገውን ደግሞ አያደርግም፡፡ ክርስቶስ ሲቆም ይቆማል ፣ ክርስቶስ ሲራመድ ይራመዳል ፣ ክርስቶስ ሲፈጥን ይፈጥናል ፣ ክርስቶስ ሲዘገይ ይዘገያል ፣ ክርስቶስ ዝም ሲል ዝም ይላል ፣ ክርስቶስ ሲናገር ይናገራል፡፡
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው እኔ ክርስቶስን እንደምከተል የሚለው፡፡
እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ። 1 ቆሮንጦስ 11:1
በጳውሎስ ውስጥ የሚኖረው ክርስቶስ እንጂ ጳውሎስ አይደለም፡፡ የጳውሎስን አይን ተጠቅሞ የሚያየው ክርስቶስ ነው ፣ የጳውሎስን እግር ጠተጠቅሞ የሚያሄደው ክርስቶስ ነው ፣ የጳውሎስን እጅ ተጠቅሞ የሚሰራው ጌታ ነው፡፡
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡27
ጳውሎስ በራሱ አነሳሽነት የሚያደርግው ነገር የለም፡፡ ጳውሎስ የሚከተለው በውስጡ የሚኖረውን የክርስቶስን እንቅስቃሴ ነው፡፡
ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ኤፌሶን 5፡30
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እፀልያለሁ ብሎ የሚናገረው፡፡ ክርስቶስ በውስጡ እንዳለ ንቁ የሆነ ሰው በውስጡ ላለው ክርስቶስ የአካል ብልት ለመሆን ይዘጋጃል፡፡ ክርስቶስ በውስጡ ለመኖር እንደሚፈልግ ያወቀና ክርስቶስ በውስጡ እንዲኖር እንዲወጣ ፣ እንዲገባ ፣ እንዲሰራና እንዲናገር ራሱን ያዘጋጀ ሰው በህይወቱ ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #በመንፈስመመላለሰ #ቃሉንማሰላሰል #መንፈስበእኛ #ህግንመፈፀም #ኢየሱስ #ቤተመቅደስ #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሔርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ #መንፈስቅዱስ

No comments:

Post a Comment