Popular Posts

Sunday, June 3, 2018

ራእይ ባይኖር

ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው። ምሳሌ 29፡18
በአጠቃላይ አነጋገር ራእይ ማለት ማየት መረዳት ማለት ነው፡፡
እንደ መፅሃፍ ቅዱስ ደግሞ ራእይ አለን ማለት ማለት እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ ማወቅ መረዳት ችለናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር እኛ እንድንሰራ የሚፈልገውን ነገር ማወቅ ማለት ነው፡፡ በህይወታችን እንድንሰራው በውስጣችን ያለ ሸክም ራእይ ይባላል፡፡ ካልሰራነው እረፍትን የማይሰጠን ሸክም ራእይ ይባላል፡፡ የህይወት ትኩረታችን ራእይ ይባላል፡፡ የህይወተ አላማችን ራእይ ይባላል፡፡ በምድር ላይ የምንኖርበት ምክኒያት ራእይ ይባላል፡፡  
በምድር ላይ የተፈጠርነው ለምክኒያት ነው፡፡ በምድር ላይ የተፈጠርነው እንደ ድንገት በእድል አይደለም፡፡ በምድር ላይ ያለነው በአጋጣሚ አይደለም፡፡
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። ኤርሚያስ 1፡4-5
በምድር ላይ የተፈጠርነው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን ስራ ለመስራት ነው፡፡ በምድር ላይ ያለነው ያገኘነውን ስራ ሁሉ ለመስራት አይደለም፡፡ በምድር ላይ ያለነው የሚያዋጣውን ስራ ሁሉ ለመስራት አይደለም፡፡ በምድር ላይ ያለነው ለእኛ የተዘጋጀውን ስራ ለመስራት ነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
እግዚአብሄር ሲፈጥረን ከስራ ጋር ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር ሲፈጥረን የመደበልን ስራ አለ፡፡ እግዚአብሄር ሲፈጥረን ለመደበልን ስራ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በመስጠት ነው፡፡ የተፈጠርነው እግዚአብሄር ለመደበልን ስራ የሚያስፈልገው ስጦታና ክህሎት ሁሉ በውስጣችን ተቀምጦ ነው፡፡ የተፈጠርነው በምድር ላይ ለተመደበልን ስራ ከሚያስፈልገው ክህሎት ሁሉ ጋር ነው፡፡
እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ማወቅ የሚያስፈልገው ስለዚህ ነው፡፡ በህይወት ራእይ እንዲኖረን የሚያስፈልገው ስለዚህ ነው፡፡  
ራእይ የምናገኘው ሁኔታዎች አይደለም፡ሸ ራእይት የምናገኘው ከወላጆቻቸነ አይደለም፡ የልጅነት ምኚታችንን አይደለም እንደራእይ የምንከተለው፡፡ሸ ራእይትን የመናገኘው በምድር ላይ ያለውን ክፍተት በማየት አይደለም፡፡
ራእይን የሚሰጠው ለራሱ ስራ አላማ የፈጠረን እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ለክብሩ ከፈጠረን ከእግዚአብሄር ብቻ ራእያችንን እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስባትን ሃሳብ ማወቅ ራእይን መቀበል ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበውን ሃሳብ ያውቃል፡፡ ከመወለዳችን በፊት የተወለድንበት ምክኒያት ነበር፡፡ ከመወለዳችን በፊት ስንወለድ የምንሰራው ስራ ነበር፡፡ የተወለድንበት ምክኒያት ልንሰራው ያለ የተመደበልን ስራ ስለነበረ ብቻ ነው፡፡
የእኛ ስራ በፀሎት ከእግዚአብሄር ራእያችንን መቀበል ነው፡፡ እግዚአብሄ ሆይ ምን እንድሰራ ነው በምድር ላይ ያለሁት ብሎ መጠየቅ የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ሃላፊነታችን ነው፡፡ የእኛ ስራ የተቀበልነው ራእይ በምድር ላይ በትጋት መፈፀም ነው፡፡
የህይወቱን ራእይ ከእግዚአብሄ ፈልጎ ያላገኘ ሰው መረን ነው፡፡ ራእይ የሌለው ሰው የት እንደሚሄድ የማያውቅ ስርአት የሌለው ሰው ነው፡፡ ራእይ የሌለው ሰው መነሻም መድረሻም ስለሌለው አያርፍም፡፡ ራእይ የሌለው ሰው የሚሄድበትን ስለማያውቅና ሲደርስ ስለማያውቅ በህይወቱ እረፍት የለውም፡፡ ራእይ የሌለው ሰው ሌላው የሚሰራውን ሊሰራ ሲሞክር ለዚያ ስላልተካነ ይወድቃል፡፡ ራእይ የሌለው ሰው ግብ ስለሌለው ፍሬያማ አይሆንም፡፡ ራእይ የሌለው ሰው አንድ ህይወቱን በከንቱ ያባክናል፡፡
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ ለአንድ ስራ እንደ ፈጠርከኝ አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ለምን እንደ ፈጠርከኝ እረዳ ዘንድ አይኖቼክ ክፈት፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አስቀድሞ የተመደበለኝን ስራ ብቻ ለመስራት እችል ዘንድ መንፈስህ ስለሚመራኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ የተለያዩ ነገሮችን አይቼ ከራእዬ እንዳልወጣ በመንፈስህ ጠብቀኝ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ራእዬን መከተል እችል ዘንድ ፀጋን ስለምታበዛልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡  በኢየሱስ ስም እፀልያለሁ፡፡ አሜን
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መረን #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment