Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, June 20, 2018

ለማይመቸን መሪ መፀለይ

በምድሪቱ ላይ ተስፋን እየታየ ነው፡፡ ብዙ ሰው መሪውን ለመደገፍ ቁርጠኝነት እያሳየ ነው፡፡ ብዙ ሰው ለመሪው ለመፀለይ ከፊት ይልቅ እየተበረታታ ነው፡፡ ይህ በርቱ ቀጥሉበት የሚያሰኝነው፡፡
ግን ግን እንደክርስትያን መሪ ሲመቸን ብቻ ነው የምንፀልይለት? መሪ ሲመቸን ብቻ ነው ድምፃችንን የምናሰማውና ለአገር የሚጠቅም ነገር የምንናገረው? መሪ ሲመቸን ብቻ ነው ከመንግስት ጋር የምንቆመው? መሪ ሲመቸን ብቻ ነው ለነገስታት የምንገዛው?
አንድ ጊዜ ቄስ በሊና ሰርቃ ሲናገሩ ያስደነገጠኝን ነገር ላካፍላቹ፡፡ ቄስ በሊና ለመንግስቱ ሃይለማርያም እፀልይለት ነበር ሲሉ ስሰማ በወቅቱ እጅግ ተገርሜ ነበር፡፡ መንግስቱ ሃይለማሪያም ኮሚኒስትን ስርአት የሚከተል ፣ እግዚአብሄር የለም የሚልና ክርስትያኑን ያሳደደ ሰው እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ነገር ግን እኝህ የእግዚአብሄር ሰው ለመንግስቱ ይፀልዩለት ነበር፡፡
እውነተኛው ክርስትና ያ ነው፡፡ ለማይመቸን መሪ በጌታ መታዘዝና መገዛት ይጠይቃል፡፡ ክርስትና ለማይመቸን መሪ መፀለይ ይፈልጋል፡፡ በክርስትና የማይመቸንን መሪ ባገኘነው አጋጣሚ በተቃውሞም ይሁን በድጋፍ ሃሳብ ከጎን መቆም ይጠበቅብናል፡፡ ከእግዚአብሄር የሚመጣውን ማንኛውም ስልጣን በምስጋና ልብ ልንቀበለው ይገባል፡፡   
ክርስትያን በመሪ የፖለቲካ ድርጅትም ይሁን በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ሆኖ አገሩን ማገልገል ይችላል፡፡ ክርስትያን በተቃዋሚ የለቲካ ድርጅት ውስጥ ሆኖ ለፍትህ ለእኩልነትና ለሰላም ሊታገል ይችላል፡፡ ነገር ግን ወደ መንግስት አሰራር ሲመጣ ግን ስልጣን ለያዘው መንግስት መገዛት ግድ ነው፡፡
ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ። ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ። በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡17-19
ለበላይ ባለስልጣን መገዛት የአገርን አንድነት ይጠብቃል፡፡ የአገርን አንድነት መጠበቅ ማለት ሁሉንም አንድ ቋንቋና አንድ ባህል አርጎ ማስተዳደር ማለት ሳይሆን ሁሉም በመሪው ስር ለአገር ብልፅግና በአንድነት እንዲሰራ ማስቻል ነው፡፡  
ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡1-7
ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ መደረጉ አገር ፀጥና ዝግ በማለት እንድታደርግ ያደርጋታል፡፡ ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ መደረጉ ፖለቲከኞች በአስተዳደሩ ፣ ጋዜጠኞች በመረጃ ልውውጥ ፣ የፀጥታና የደህንንት ተቋማት ወታደራዊና በመረጃ እውቀት አገራችውን እንዲያገለግሉ ሙስናም እንዲዋጉ ፍትህ እንዲሰፍንና የበለፀገች አገርን ለመፍጠር ጉልበት ይሰጣቸዋል፡፡ ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ መደረጉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም የመንግስትን ሃይልን ያለአግባብ መጠቀምን እንዲከታተሉና እንዲያጋልጡ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1 ወደ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
እንደአሁኑ ደስ ደስ ሲለን ብቻ ሳይሆን ሲከፋንም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ መፀለይን እንርሳ፡፡ እግዚአብሄርን የምናውቅ እኛ ለክፉ መሪ ካልፀለይን ፣ ከክፋት ካልጠበቅነውና ካልተዋጋንለት ለማን እንተወዋለን፡፡  እግዚአብሄር መሪን እግዚአብሄር ይመራዋል ብለን የምናምን እኛ ለክፉ መሪ በመታዘዝ ምሳሌ ካልሆንን ማን ሊታዘዘው ይችላል፡፡ 
የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። መጽሐፈ ምሳሌ 21፡1
እግዚአብሄርን የምናምን እኛ ለማይመቸን መሪ ካልፀለይንና ካልጠበቅነው ለክፉ አሳልፈን እንሰጠዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ተስፋ የምናደርግ እኛ ፍትህ ሲዛባ ድምፃችንን ካላሰማን ማን ሊያሰማ ይችላል ብለን እንጠብቃልን?
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ተቃውሞ #ሃዘን #ምልጃ #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment