Popular Posts

Follow by Email

Friday, June 15, 2018

ሲሆን ህልም ተራ

አንዳንድ ሰው ሲናገር ስትሰሙት ህልሙ ተራ እንደሆነ በግልፅ ያስታውቃል፡፡ አንዳንድ ሰው ሲናገር ስትሰሙት እይታው ቅርብ እንደሆነ ቃላቶቹና በህይወቱ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች ያሳብቁበታል፡፡  
ኢየሱስ ወደምድር ሲመጣ በጨለማ የነበርነውን እኛን ማየት የማንችለው የነበርነውን እኛን ብርሃን ሰጠን፡፡ ኢየሱስ ህይወታችንን ለመለወጥ በምድር ላይ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ እይታችን ከምድር አንስቶ ሰማይ ላይ እንዲሆን ማድረግ ነበር፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ የማቴዎስ ወንጌል 6፡19-20
ሰው የኢየሱስን ትመህርት ሰምቶ ምኞቱ ፣ ፍላጎቱና ህልሙ ካልተቀየረ የኢየሱስ ትምህርት አልገባውም ማለት ነው፡፡ ሰው ኢየሱስን አይቶ እይታው ካልተስተካከለ እምነትን አልተረዳም ማለት ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 2 የጴጥሮስ መልእክት 19
መፅሃፍ ቅዱስ እይታችንን ከማስተካከል አንፃር ያስተማረውን ጥቂት ነገሮች እንመልከት፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለን ከሚል አጭር እይታ እንድንድን ያስተምራል፡፡
ክርስቶስን ሳንረዳ ተስፋ አልበነረንም፡፡ ተስፋችን ዛሬን መደሰት አለማችንን መቅጨት ነበር፡፡ በአለም ያለ ሰው የሚያየው ዛሬን ብቻ  ነው፡፡ በአለም ያለ ሰው ነገሮችን የሚመዝነው በዛሬ ጥቅሙ ነው፡፡ በአለም ያለ ሰው ነገሮችን የሚያየው ለዛሬ በሚያገኘው ጥቅም ብቻ ነው፡፡
በአለም ያለ ሰው ምድርን እንደ ጊዜያዊ ስፍራ ማየት አይችልም፡፡ በአለም ያለ ሰው ምድርን እንደመተላለፊያ ማየት አይችልም፡፡ በአለም ያለ ሰው ምድርን እንደጊዜያዊ ድንኳን ማየት አይችልም፡፡ አለማዊ ሰው ያለው ይህ ህይወት ብቻ ነው፡፡ አለማዊ ሰው እኔ የሚጠይቀው ከዚህ ነገር ምን አገኛለሁ የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ አለማዊ ሰው ከራሱ በስቲያ የሚያየው ጌታ ስለሌለ ያለውን ህይወት እንደፈለገ ያደርገዋል፡፡ አለማዊ ሰው ጌታ ኢየሱስ ጌታው ስላይደለ የራሱ ጌታ ራሱ ነው፡፡
በአለም ያለ ሰው በዘላለም ህይወት አእምሮ መኖር አይችልም፡፡  በአለም ያለ ሰው ነገሮችን በዘላለም ህይወት ሚዛን መመዘን አይችልም፡፡ በአለም ያለ ሰው ነገሮችን በዘላለም ህይወት እይታ ማየት አይችልም፡፡ በአለም ያለ ሰው አንድ ቀን በእግዚአብሄር ፊት እንደሚጠየቅ ሰው በሃላፊነት ስሜት ሊኖር አይችልም፡፡
አእምሮው ያልታደሰም ሰው እንዲሁ ዳግም ይወለድ እንጂ ነገሮችን የሚያየው አለማዊ ነገሮችን እንደሚያየው ነው፡፡ አእምሮው ያልታደሰ ሰው ምድርን እንደጊዜያዊ መተላፊያ መንገድ ሊያይ አይችልም፡፡ አእምሮው በእግዚአብሄር ቃል ያልታደሰ ሰው በዘላማዊ ህይወት እይታ ነገሮችን ሊመዝን አችልም፡፡ አእምሮው ያልታደሰ ሰው ከሞት ተነስቶ በእግዚአብሄር ፊት እንደሚጠየቅ በሃላፊነት ስሜት እግዚአብሄርን በመፍራት ሊኖር አይችልም፡፡
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡32
አእምሮው ያልታደሰ ሰው የሚያስበውና የሚያልመው ከማንኛውም ነገር ውስጥ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ ነው፡፡ አእምሮው ያልታደሰ ሰው የሚያስበው በእግዚአብሄር መንግስር ላይ ምን እንደሚዘራ ምን ኢንቨስት አንደሚያደርግ አያስብም፡፡ አእምሮው ያልተለወጠ ሰው የሚያስበው እርሱ ስለሚበዛለት ጥቅማጥቅም እንጂ የእግዚአብሄር ህዝብ ስለሚያገኘው በረከት መለወጥና መሻገር አይደለም፡፡ አእምሮው በእግዚአብሄር ቃል ያልታደሰ ሰው ካለው የምስኪንነት አስተሳሰብ የተነሳ ከምንም ነገር ውስጥ ምን እንደሚያገኝ ነው፡፡ አእምሮው በእግዚአብሄር ቃል ያልታደሰ ሰው ምን እንደሚሰጥ ፣ ምን እንደሚባርክና ምንን እንደሚጠቅም አያስበውም፡፡ አእምሮው ላልታደሰ ሰው አምላክ ሆድ እንጂ እግዚአብሄር አይደለም፡፡ አእምሮው በእግዚአብሄር ቃል ያልተለወጠ ሰው አሳቡ ምድራዊ ነው፡፡   
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡19-20
አእምሮው ያልታደሰ ሰው የእግዚአብሄርን መንግስትር እና የእግዚአብሄርን ቤተክርስትያን የሚያየው እንደ ቤተሰብ ሳይሆን እንደመጠቀሚያ መንገድ ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በላይ ያለውን እንጂ በምድር ያለውን እንዳንፈልግ ያስተምረናል፡፡
እይታችን ከሙታን እንደተነሱ ሰዎች በምድር ላይ ከቀረ በክርስትና ህይወታችን ውጤታማ አንሆንም፡፡ እይታችን በሰማያዊ ስፍራ እንደተቀመጡ ሰዎች ካልሆነ ህይወታችን ከማያምኑት የማይሻል ይሆናል፡፡ እይታችን በሰማያዊው ስፍራ በመንፈሳዊው በረከት ሁሉ እንደተባረከ ሰው ካልሆነ እግዚአብሄር በልቡና በነፍሱ እንዳለ ፈቃዱን በምድር ፈጽፅመን ማለፍ እንችልም፡፡
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡1-2
መፅሃፍ ቅዱስ እንደ አህዛብ የሚበላና የሚጠጣ በመፈልግ ህይወታችንን እንዳናባክን ያስተምረናል፡፡
እኛ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እኛ በራሳችን አይደለንም፡፡ እኛ አምላክ አለን፡፡ እኛ የሚያስፈልገንን ነገር የሚያቀርብልን አባት አለን፡፡ የእኛ አላማ አባታችን ከእኛ የሚፈልገውን ነገር በማድረግ እርሱን ማስደሰት እንጂ ይጨመርላችኋል ያለውን የሚበላና የሚጠጣ በመፈለግ አይደለም፡፡ እይታችን ከአህዛብ ካልበለጠ ለእግዚአብሄር ጠቃሚ ልንሆን አንችልም፡፡ እይታችን የሚበላና ከሚጠጣ መፈለግ አልፎ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን በመፈለግ ላይ ካልሆነ በክርስትና ህይወታችን እንከስራለን፡፡  
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡31-33
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #ተስፋ #መፀለይ #መንፈስ #በረከት #መዝገብ #ሰማይ #እንግዶች #ዘላለም #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እይታ #ምድራዊ #ሰማያዊት #ማየት #ቅርብ

No comments:

Post a Comment