Popular Posts

Saturday, June 30, 2018

በህይወቴ የምጠላው

በህይወቴ የምፈራው ሞትን አይደለም፡፡ ሞት የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ሞት የሚያስፈራው የጌታ ኢየሱስን አዳኝነት ላልተቀበለ ሰው ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለያያ መንገድ ስለሆነ ያስፈራል፡፡ ሞት የሚያስፈራው ከሞት ፍርሃት ነፃ ላልወጣ ላልዳነ ሰው ነው፡፡   
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ወደ ዕብራውያን 2፡14-15
የስጋ ሞት ከምድራዊ ህይወት ወደ መንፈሳዊ ህይወት የምንሸጋገርበት መተላለፊያ በር ነው፡፡ በእውነት ካሰብነው እግዚአብሄር በሰማይ ያዘጋጀልንን ክብር ካየነው መሞት ያስደስታል እንጂ አያስፈራም፡፡ መሞት እንዲያውም እረፍትና ጥቅም ነው፡፡ በምድር የምንኖረው የእግዚአብሄርን መንግስት ለመስራት እንጂ ለእግዚአብሄር ስራ ባይሆን ኖሮ መሞት እረፍት ነው፡፡
ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1፡21-23
በህይወቴ የምፈራው ማጣትን አይደለም፡፡
ማጣት እንደማይገድል አይቸዋለሁ፡፡ ማጣት ሊፈራ የሚገባ እንዳይደለ አይቼዋለሁ፡፡ ማጣት ማንንም መንከስ እንደማይችል እንደታሰረ ውሻ ባዶ ጩኸት መሆኑን በህይወቴ አይቼዋለሁ፡፡ ማጣት የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈፀም እንደማያግድ አይቼቸዋለሁ፡፡ ዋናው ነገር ማጣት ወይም ማግኘትን ሳይሆን ሁሉንም የሚያስችለን ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስ ካለ ተጨማሪ ነገር አያስፈልገንም፡፡ ክርስቶስ ካለ ማጣት አያቆመንም፡፡ የሚያስችለን ማግኘት ሳይሆን ክርስቶስ ነው፡፡ በክርስቶስ ሁሉን እንችላለን፡፡
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11-13
በህይወቴ የምፈራው ድካምን አይደለም፡፡
ስንደክም ስንዋረድ በድካምና በመዋረድ ውስጥ ክብር አለ፡፡ በራሳችን ስንደክም ያን ጊዜ በክርስቶስ ሃይል ሃይለኛ ነኝ፡፡ የእግዚአብሄር ጉልበት በድካሜ ስለሚታይበት በድካሜ ደስ ይለኛል፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡9-10
በህይወቴ የምፈራው ሃዘንን አይደለም
ሃዘንተኛን በማፅናናት የተካነ የመፅናናት አምላክ እግዚአብሄር አባቴ ነው፡፡ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ሰላም የሚሰጥ እገዚአብሄ አብሮን ነው፡፡
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡3
በህይወቴ የምፈራው መከራን አይደለም
ፈተና እኛን አሻሽሎን አበርትቶን ከፊት ይልቅ አሳድጎን ነው የሚያልፈው፡፡ ከምንችለው በላይ እንድንፈትን የማይፈቅድ ታማኝ እግዚአብሄር ስላለ መከራን አያስፈራንም፡፡ መከራ የሚያገኘው በእኛ ላይ ያለን የማያስፈልግ ስጋዊነትነ ብቻ ነው፡፡ መከራ የሚያራግፈው ክርስቶስን የማይመስለውን የስጋ ምኞታችንን ብቻ ነው፡፡ ስጋዊነትን በሰዎች ህይወት ስናይ እንደሚቀፈን ሁሉ ለእግዚአብሄር የማይመቸው በመከራ የሚራገፈውን ስጋዊነትን ስናይ እግዚአብሄር ይመስገን ልንል ይገባል፡፡
ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። የያዕቆብ መልእክት 1፡2-4
መውጫውን ያዘጋጀው እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ስላለ ፈተና አያስፈራም፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13
የሚያስፈራው የእግዚአብሄርን ሃሳብ መጣስ ነው፡፡ የሚያስፈራው የምድር ህይወታችንን ለጊዜያዊ ለግል ጥቅማችን ማሳለፍ ነው፡፡ የሚያስፈራው ዋጋቸውን በምድር ተቀብለዋል መባል ነው፡፡ የሚያስፈራው በህይወታችን ዘመን ሁሉ እግዚአብሄር ያላለንን ነገር ሲያደርጉ በመኖር ህይወትን ማባከን ነው፡፡ የሚያስፈራው እግዚአብሄር ያዘዘንን ትተን እግዚአብሄር ያላዘዘንን ነገር ማድረግ ነው፡፡ የሚያስፈራው እግዚአብሄር ያልጠራንን ነገር በማድረግ አንዱን ህይወታችንን ማባከን ነው፡፡ የሞያስፈራው እግዚአብሄር ሳያዘን አንድ እርምጃን መራመድ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #መዳን #እምነት #ማስተዋል #አላማ #ግብ #የምፈራው #የምጠላው #ማጣት #ሃዘን #ፈተና #ሞት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ማሰብ #መሪ

No comments:

Post a Comment