Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, June 5, 2018

ቀን በደመና አምድ ሌሊት በእሳት አምድ


ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር። ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር። ዘኍልቍ 9፡17-23
እግዚአብሄር የእስራኤል ህዝብን ከግብፅ ምድር ሲያወጣና ወደተስፋይቱ ምድር ለማስገባት በትጋት ይመራቸው ነበር፡፡ እግዚአብሄር ለግምት አልተዋቸውም ነበር፡፡ እግዚአብሄር በየቀኑና በየሰአቱ ይመራቸው ነበር፡፡ እግዚአብሄር በራሳቸው የአየር ሁኔታ እውቀት እንደኖሩ አልተዋቸውም፡፡ ምክኒያቱም የሰው ምንም ያህል እውቀት የእግዚአብሄርን መንገድ ሊያውቀው አይችልም፡፡
አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ኢሳይያስ 55፡8-9
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ እንዲሳካልን በመንገዳችን ሁሉ የእርሱን መሪነት እውቅና እንድንሰጥ በመሪነቱ ሙሉ ለሙሉ እንድንታመንና መሪነቱን ብቻ እንድንከተል የሚያስተምረን፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ ምሳሌ 3፡5-7
የእስራኤል ህዝብ የሚሄድበትን መንገድ ካለእግዚአብሄር ማንም እንደማያውቀው ሁሉ እግዚአብሄር ካልመራን በስተቀር እግዚአብሄር ለህይወታችን ያለውን አላማ በአእምሮዋችን ማወቅ አንችልም፡፡ የእግዚአብሄርን ምሪት ሳንከተል ይሳካልናል ማለት ምንም መንገድ በሌለበት በምድረበዳ መቅበዝበዝ ነው፡፡ ሰው እንደ ድንገት አይሳካለትም፡፡ በእግዚአብሄር መንገድ እንዲሳካልን የእግዚአብሄርን ምሪት መከተል አማራጭ የለውም፡፡
ልጆች ሆነን እቃ ሲጠፋብን የጠፋብንን እቃ አቅጣጫውን ለማግኘት ምራቃችንን እጃችን ላይ እንተፋና በሌላው እጃችን እንመታዋለን፡፡ ምራቁ የተፈናጠረበት ቦታ ትክክለኛ እቅጣጫ ነው ብለን እድላችንን እንሞክራለን፡፡ የእግዚአብሄር ነገር ግን እንደዚያ አይደለም፡፡  
ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር። ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና። ዘፀአት 40፡36-38
የእስራኤል ህዝብ ለእግዚአብሄር መሪነት ራሳቸውን የሰጡ ነበሩ፡፡ ደመናው ካልተንቀሳቀሰ አይንቀሳቀሱም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሳይናገረን አንድን እርምጃ መውሰድ በራስ ማስተዋል መደገፍ ነው፡፡ እግዚአብሄር እስኪናገረን እርምጃን ላለመውሰድ መፍራት እግዚአብሄን ያከብረዋል፡፡  
የእስራኤል ህዝብ በራሳቸው ማስተዋል አይደገፉም ነበር፡፡ ደመናው ለአንድ ሰአትም ፣ ለአንድ ቀንም ፣ ለአንድ ሳምንትም ወይም ለአንድ ወርም ይቆይ ከደመናው ስር ይቆዩ ነበር፡፡ አምዱ ሁልጊዜ ስለሚመራቸው ሌሊትም ይሁን ቀን በተነሳ ፊዜ አብረው ይነሱ ነበር፡፡ ሌሊትም ይሁን ቀን አምዱ በቆመ ጊዜ በሰፈራቸው ይሰፍሩ ነበር፡፡  
እግዚአብሄር ደመናውን የሰጣቸው ለመሪነት ብቻ ሳይሆን ደመናው ባለበት ሲጓዙ ከሚጎዳ ጠራራ ፀሃይ እንዲድኑ ነበር፡፡ እግዚአብሄር የእሳቱን አምድ የሰጣቸው ለመሪነት ብቻ ሳይሆን የሚሄዱበትን መንገድ ብርሃን እንዲሰጣቸው በጨለማ ከመጓዝ እንዲድኑ ነበር፡፡ ደመናውን አንከተልም ቢሉ ግን እግዚአብሄርን ይስቱታል፡፡ የእሳቱን አምድ ባይከተሉት እግዚአብሄር ለህይወታቸው ካለው የእግዚአብሄር ሃሳብ ጋር ይተላለፋሉ እንዲሁም የእግዚአብሄር ጥበቃ በእነርሱ ላይ አይሆንም፡፡
እኛ እግዚአብሄር እንዲመራን ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር ሊመራን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ሊመራን አብሮን ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ እኛን ከመምራት ፈቀቅ ብሎ አያውቅም፡፡  
በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ። የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም። ዘፀአት 13፡21-22
እንዲያውም በአዲስ ኪዳን ወደ እውነት ሁሉ ሊመራን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ አለ፡፡
ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። ዮሃንስ 16፡13
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የደመናአምድ #የእሳትአምድ #ይጓዙ ##ይሰፍሩ #እስራኤል #ምድረበዳ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሔርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment