Popular Posts

Saturday, June 16, 2018

አባትን አባት የሚያደርገው

አባትን አባት የሚያደርገው በፆታ ወንድ መሆን አይደለም፡፡ አባትን አባት የሚያደርገው ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ መሆን አይደለም፡፡ አባትን አባት የሚያደርፈው ሃላፊነት መውሰድ ነው፡፡
አባትን አባት የሚያደርገው ለሚወስደው ማንኛውም እርምጃ ሃላፊነትን መውሰዱ ነው፡፡ አባትን አባት የሚያደርገው በህይወቱ የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን እግዚአብሄርን መፍራቱ ነው፡፡ አባትን አባት የሚያደርገው በህይወቱ የማይገባውን ነገር ልጆቹ ላይ አለማድረጉ ነው፡፡ አባትን አባት የሚያደርገው ትክክለኛውን ነገር ማድረጉ ነው፡፡
አባትን አባት የሚያደርገው ራሰ ወዳድ አለመሆኑ ነው፡፡
አባትነት መስጠት ማካፈል ነው፡፡ ለመስጠትና ለማካፈል አባት የፍቅር ሰው መሆን አለበት፡፡  
አባትነት አባት የሚያደርገው ልጆቹን በትህትና ማገልገሉ ነው፡፡
አባትነት የመጠቀሚያ ስልጣን ሳይሆን የማገልገያ እድል ነው፡፡ አባት ልጆቹን በማገልገል መምራት ይገባዋል፡፡ አባት ልጆቹን በትጋትና በታማኝነት መምራት አለበት፡፡  
አባትን አባት የሚያደርገው የልብ ስፋቱ ነው፡፡
አባት ልጆቹ ከእርሱ የተለዩ እንደሆኑ መቀበል አለበት፡፡ አባት ልጆቹን ለማሳደግ ከእግዚአብሄር በአደራ የተቀበላቸው እንጂ የራሱ እንዳልሆኑ ማወቅ  አለበት፡፡ አባት እግዚአብሄር በልጆቹ ውስጥ ያለውን አላማ መፈለግ መረዳትና ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ አባት ያልተፈፀሙትን የራሱን ህልሞች በልጆቹ ህይወት ለመፈፀም መሞከር የለበትም፡፡ አባት ልጆቹ የራሳቸውን ራእይና ህልም ማክበር አለበት፡፡ አባተ ከእርሱ የተለዩ ልጆቹን በሰፊ ልብ መቀበል አለበት፡፡
አባት ልጆቹ ልጅ እንዲሆኑ መፍቀድ አለበት፡፡ አባት ራሱ ትልቅ ስለሆነ ልጀቹን እንደትልቅ አይቶ ማስጨነቅ የለበትም፡፡ አባት ከልጆቹ ከአቅማቸው በላይ የፍፁምነት ደረጃ በመጠየቅ ልጆቹን ማስቆጣት የለበትም፡፡
እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን . . . እንጂ አታስቆጡአቸው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡4
አባትን አባት የሚያደርገው ልጆቹን ኮትኩቶ በማሳደጉ ነው
አባት ልጆቹን በትግስት መኮትኮትና ማሳደግ አለበት፡፡ አባት ለልጆቹ  እድገት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድርግ በመጀመሪያ ራሱን ማሳደግ ከዚያም ልጆቹን ለማሳደግ መትጋት አለበት፡፡ አባት ልጆቹ ያላደጉበትን የህወይት ክፍል እየተከታተለ ለእድገታቸው የሚያስፈልገውን ትምህርትና ልምድ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡   
አባትን አባት የሚያደርገው ለባለቤቱ ለእግዚአብሄር እውቅና መሰጠቱ ነው፡፡
ልጆች የእግዚአብሄር ስጦታዎች ናቸው፡፡ ልጆች የእግዚአብሄር ፍጥረት ናቸው፡፡ ልጆችን የምናሳደገው ለእግዚአብሄር ነው፡፡ ልጆችን ስናሳድርግ የእኛም የእነርሱም አባት እንዳለ እውቅና በመስጠት መሆን አለበት፡፡ ልጆችን ስናሳድግ እኛ ለልጆቻችን አባት ብቻ ሳንሆን ለእግዚአብሄርም ልጆች እንደሆንን መዘንጋት የለብንም፡፡
ልጆችን ስናሳድግ እግዚአብሄር ለልጆች የራሳቸውን በጀት እንደሚያመጣ ማመን አለብን፡፡ ልጆችን ስናሳድግ እንደ ፍላጎታችን ሳይሆን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ማሳደግ ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። ትንቢተ ሚልክያስ 2፡15
አባትን አባት የሚያደርገው በሃሳብ በንግግርና በድርጊት ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡
አባትነት የ 24 ሰአት የ7 ቀን ሃላፊነት ነው፡፡ አባትነት መናገር ማስተማር ብቻ ሳይሆን መኖርን ይጠይቃል፡፡ አባት እንዲያውቁትና እንዲከተሉት ለልጆቹ ጊዜን መስጠት ይገባዋል፡፡ ልጆች ከንግግር በላይ ኑሮን ይኮርጃሉ፡፡ አባትነት በአስተሳሰብ በአነጋገርና በድርጊት ለልጆች መልካም ምሳሌ መሆን ነው፡፡
አባትን አባት የሚያደርገው በትጋት መቅጣቱ ነው፡፡
አባትነት መኮትኮት ማሳደግ መምራትንና መቅጣትን ይጨምራል፡፡ ልጅን ለመቅጣትና ለማረም የተሻለው ሰው አባት ነው፡፡ አባት ልጆቹን ለማስተማር ለመከተታልና ለመቅጣት ከተጋ ልጆቹን ማዳን ይችላል፡፡ አባተ ግን ልጆቹን ለመቅጣት ከሳሳ ስለ ልጆቹ በክፉ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤቱ ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3፡13
እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። ወደ ዕብራውያን 12፡10-11
እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡4
አባትን አባት የሚያደርገው ይቅርታና ምህረት ማድረጉ ነው፡፡
አባት አንዳንዱን የልጆችን ጥፋት የሚያልፍ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አባት የምህረት አስተማሪ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አባት ይቅር የሚል የይቅርታ ልብ ያለው ሊሆን ይገባዋል፡፡
አባትነት ጥበቃና እንክብካቤ ነው፡፡
አባት ልጆቹን ለክፋት አሳልፎ የማይሰጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አባት ልጆቹን ከተግዳሮት ለመከላከል ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ችግር ወደልጆች ላይ ከሚመጣ አባት ራሱ ዋጥ የሚያደርገውና ቤተሰቡን የሚጠብቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አባት የነገሮችን አካሄድ በትጋት የሚከታተል አደጋን ከሩቅ የሚያይ ትጉህ ጠባቂ ሊሆን ይገባዋል፡፡
አባት ምሪትን የሚሰጥ ሊሆን የገባዋል
አባት  ስለቤተሰቡ እግዚአብሄርን የሚሰማ ልጆቹን የሚመራ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አባት በእግዚአብሄር ምሪት ላይ የሚደገፍ ልጆቹን ሊደገፉበት የሚችሉ የመርህ ሰው ሊሆን ይገባዋል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
መልካም የአባቶች ቀን!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወላጅ #ፍቅር #አባት #እርማት #ጥንካሬ #ራእይ #ደረጃመስጠት #ጥላ #ማበረታታት #አባትነት #ተግሳፅ  #መሪ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment