Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, June 12, 2018

ራሳችሁን ጠብቁ

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። የይሁዳ መልእክት 1:21
ባሳለፍኩት በክርስትና ህይወቴና በአገልግሎት ዘመኔ ከምንም ነገር በላይ ራስን መጠበቅ ወሳኝ ነገር እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ነገሮች ይመጣል ይሄዳሉ፡፡ ሰው ይነሳል ይወድቃል፡፡ ችግር ይነሳል ያልፋል፡፡ ሃዘን ይመጣል ያልፋል፡፡ የሚቀረው እኔና እኔ ብቻ ነን፡፡  
ከምንም ነገር በላይ ራስን መጠበቅን የመሰለ ነገር የለም፡፡
እግዚአብሄር በሃይል የሚጠቀምባቸው ሰዎች ሲወድቁ አይቻለሁ፡፡ ጌታን አገልግለው የማይጠግቡ ሰዎች እሳታቸው ጠፍቶ አይቻለሁ፡፡ ሰውን አገልግለው የማይጠግቡ ሰዎች ሁሉ ነገር ጠፍቶባአቸው አይቻለሁ፡፡ አማኝ የነበሩ ሰዎች የማያምንና ክፉ ልብ ሲኖራቸው አይቻለሁ፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ ወደ ዕብራውያን 3፡12-13
ሰው ራሱን ካልጠበቀ በአገልግሎት አይፀናም፡፡ ካልተጠነቀቀ የማይወድቅ ሰው የለም፡፡ ካልተጠነቀቀ በስተቀር ከመውደቅ ያለፈ ውድቀት ሊነካው የማይችል ሰው የለም፡፡ ላለመጣል ዋስትና ያለው ሰው ማንም የለም፡፡  
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27
ሰዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚወድቁት ራሳቸውን ስላልጠበቁ ነው፡፡ ሰዎች አንድ ጊዜ ታይተው ያባሩት ራሳችውን ለመጠበቅ ስላልተጉ ነው፡፡ ሰዎች ታይተው የከሰሙት ራሳችውን ከመጠበቅ በላይ ለሌላ ነገር ቅድሚያ ስለሰጡ ነው፡፡ ሰዎች እንደዚህ የተጣሉት ራሳችሁን ጠብቁ የሚለውን የእግዚአብሄርን ቃል ምክር ቸል ስላሉ ነው፡፡ ሰዎች እንደዚህ ከአገልግሎት የተጣሉት እኔ ላይ አይደርስብኝም ከሚል አጉል በራስ መተማመን ስሜት ነው፡፡
ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ መጽሐፈ ምሳሌ 2፡11
ቸልተኛን ሰው ሊውጥ በተጠንቀቅ የቆመና የተዘጋጀ ጠላት አለ፡፡
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡8
መፅሃድ ቅዱስ ራሳችሁን ጠብቁ ሲል እሺ ጌታዬ ማለትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ ራሳችሁ ጠብቁ ሲል የተሻለ እንደምናውቅ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ ራሳችሁን ጠብቁ ሲል ካልመሰለን አይናችን አያየ እንወድቃለን፡፡
እስካሁን በአገልግሎት ያለኸው ራስህን ስለጠበቅክ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በአገልግሎት የምትቀጥለው ራስህን ከጠበቅህ ብቻ ነው፡፡ አገልግሎት የሚመጣው ራስን ከመጠበቅ ነው፡፡ አገልግሎታችን የሚዘልቀው ራሳችንን በመጠበቅ ስንዘልቅ ነው፡፡ ራሳችንን ለመጠበቅ ቸል ስንል ሁሉም ነገር ከእጅ ያመልጣል፡፡  
ለማዘንና ለመማረር ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ሰውን ለመጥላት ብዙ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ሰውብን ለመናቅ ብዘዙ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ጥላቻ ንቀትና ምሬት በተሞላ አለም ውስጥ እንኖራለን፡፡ ካልተጠነቀቅን ጥላቻ ንቀትና ምሬትን በቀላሉ ከሌሎች ሊጋባብን ይችላል፡፡
ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፡18-19
ራሳችን የምንጠንቀው በእግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ሊጠብቀን የሚችለው ብቸኛው ነገር የእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ጥላቻ ክፋትና ምሬት በስተው ሊገቡ የማይችሉት የእግዚአብሄርን ፍቅር ብቻ ነው፡፡  
በእግዚአብሄር ፍቅር ከጥላቻ እንጠበቃለን፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቅር ካሰብን ምህረትን እናደርጋለን፡፡ ጠላታችንን የምንወደው በእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ የማንሰናከለው የሚያሰናክል ነገር ስለሌለ አይደለም፡፡ የማንሰናከለው በእግዚአብሄር ፍቅር ራሳችንን ስለምንጠብቅ ነው፡፡ የማንሰናከለው የህይወት መንገሰዳችንን በጥንቃቄ ስለምንፈትሽ ነው፡፡ የማንሰናከለው ረጋ ብለን መንገዳችንን በጥንቃቄ ስለምንመርጥ ነው፡፡
እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 18፡33-35 
ሁኔታውን ሁሉ ወደ ውስጡ የሚያስገባ ሰው በህይወትም በአገልግሎትም አይፀናም፡፡ የሚመጣውንና የሚሄደውን ሁሉ ወደውስጡ የሚያስገባ ሰው በአገልግሎት መቀጠል ይከብደዋል፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ራሱን የማይጠብቅ ሰው ለጠላት ጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡
በእግዚአብሄር ፍቅር ራሱን የማይጠብቅ ሰው ከህጉ ውጭ እንሚጫወት ተጫዋች ነው፡፡ በእግዚአብሄ ፍቅር ራሱን የማይጠብቅ ሰው ማሸነፉን እንጂ በህጉ መጫወቱን ጥንቃቄ እንደማያደርግ ሰው ነው፡፡  
የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡4-5
በእግዚአብሄር ፍቅር ሁኔታዎች ውስጣችን ገብተው እንዲያስጨንቁን በውጭ እናስቀራቸዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ሁኔታዎችን በውጭ እንጠብቃቸዋለን፡፡ ጥላቻ እንዳያሳድፈን በእግዚአብሄር ፍቅር ራሳችንን እናነፃለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር እሳታችንን እንጠብቃለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር የአገልግሎት ቅናታችንን ጠብቀን እናቆያለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር የአገልግሎት ቅባታችንን እናቆያለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ፀጋችንን ለረጅም ጊዜ እናዘልቀዋለን፡፡
የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ 1ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ወደ ዕብራውያን 12፡15-16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

#ኢየሱስ #ጌታ #ራስ #ራስህን #ጠብቅ #ለራስህ #ተጠንቀቅ #ቃል #ህይወት #አገልግሎት #አምልኮ #ፀሎት #ጥሪ #ተመልክተን #መቃጠል #መቀጣጠል #ክብር #አገልግሎት #መዋረድ #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment