Popular Posts

Saturday, June 30, 2018

የጴጥሮስ ክህደት

ብዙ ጊዜ ስለክህደት ሲነሳ ስሙ የሚነሳው ይሁዳ ነው፡፡ እንዲያውም የክህደት ሌላ ስሙ እስኪመስል ድረስ ይሁዳ ከክህደት ጋር አብሮ ይነሳል፡፡
ኢየሱስን ከካዱት ሁለት ሰዎች መካከል ይሁዳና ጴጥሮስ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጴጥሮስም ይህን ሰው አላውቀውም ብሎ ክዶዋል፡፡
ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ፦ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት፦ ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች። ዳግመኛም ሲምል፦ ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ። የማቴዎስ ወንጌል 26፡69-72
ኢየሱስ ሰውን ሊክደው እንደሚችል ያውቃል፡፡ ሰው ሊክደኝ አይችልም ማለት አደገኛ አመለካከት ነው፡፡ ሰው የሚክደን በራሱ ችግር እንጂ እኛ ስላጠፋንም አይደለም፡፡ ሃጢያት የሌለበት ኢየሱስ ተክዷል፡፡
ልካድ እችላለሁ ብሎ ልብን ማስፋት ብንካድ ጉልበት ሊሰጠን የሚችል ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሰው ሊካድ ቢችልም ሰውን ማመን ታላቅ ልብ ነው፡፡ ሰው ሊክደኝ ይችላል በሚል ፍርሃት ሰውን ማመን የሚያቆም ሰው ብቻውን ይቀራል፡፡ ሊክድ የሚችል እንዳለ የታመነ የማይክድ ሰውም ደግሞ አለ፡፡ ሊክድ በሚችለው ፍርሃት የታመነውን ሰው ማጣት ጥበብ አይደለም፡፡  
ፍቅር . . . ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡7
ይሁዳ ሊክደው እንደሚችል ኢየሱስ አውቆ ነበር፡፡ ኢየሱስ እንደሚክደው አውቆ ከይሁዳ ጋር አብሮት ኖሮዋል አብሮት አገልግሏል፡፡
ኢየሱስም፦ እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው። ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና። የዮሐንስ ወንጌል 6፡70-71
ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደውም ሁሉ አስቀድሞ አውቆዋል፡፡
እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። የሉቃስ ወንጌል 22፡33-34
ይሁዳ በክህደቱ አገልግሎቱንም ህይወቱንም አጣ፡፡
በመዝሙር መጽሐፍ፦ መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም፦ ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአልና። የሐዋርያት ሥራ 1፡20
ማንም ሰው ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሰው በክህደቱ ከቀጠለ ህይወቱንና አገልግሎቱን ያጣል፡፡ ሰው ግን በክህደቱ ካዘነና ከተመለሰ እንዳልወደቀ ሆኖ እግዚአብሄር እንደገና በሃይል ይጠቀምበታል፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡10
ከይሁዳ የሚለየው ጴጥሮስ የሚመለስ ልብ ነበረው፡፡ አንዳንዴ ካልሆነ የጴጥሮስ ክህደት አይነሳም፡፡ የጴጥሮስ ክህደት ከመረሳቱ የተነሳ ጴጥሮስን የምናስታውስበት ብዙ መልካም ነገሮች አሉ፡፡ ኢየሱስ የጴጥሮስን ከውድቀቱ ባሻገር መነሳቱን አይቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ ከክህደቱ ባሻገር የጴጥሮስን ጠቃሚነቱን አይቶ ነበር፡፡
ጴጥሮስ የሚሰበር በጥፋቱ የሚያዝን ልብ ስልነበረው እግዚአብሄር ሁለተኛ እድል ሰጠው፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስ ወደፊት የማይክድበትን መንገድ ቀየሰ፡፡ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላና እንዲክድ ያደረገውንና ያሸነፈውን የፍርሃት መንፈስን የሚያሸንፍበት መንፈስ ቅዱስ ተሞላ፡፡
ጴጥሮስ በንስሃ ከተመለሰ በኋላ መንፈስ ቅዱስን በመሞላት ያሸነፈውን የፍርሃትን መንፈስ አሸነፈው፡፡
ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። የሐዋርያት ሥራ 2፡14
ጴጥሮስ ሲመለስ እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሃይል የፍቅር ራስን የመግዛት መንፈስ ሰጠው፡፡
እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡7
ማንም ሰው በክህደት ሊወድቅ ይችላል፡፡ የሚነሳውና እንደገና የእግዚአብሄር መጠቀሚያ የሚሆነው ሰው ግን በንስሃ በእግዚአብሄር ፊት የሚመለሰው ሰው ብቻ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መካድ #መታለል #ታማኝነት #ክህደት #ንስሃ #ሃዘን #መመለስ መጣል #መሰደድ #መገፋት #መውደቅ #አለመመረጥ #ተቀባይነትማጣት #ዋጋአሰጣጥ #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አምልኮ #እምነት #መከተል 

No comments:

Post a Comment