Popular Posts

Wednesday, August 8, 2018

ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ

እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16
ሃጢያት ያታልላል፡፡ ሃጢያትን የሚሰራ ሰው አሁን ሃጢያት እይሰራሁ ነው ብሎ ላያስብ ይችላል፡፡ ሃጢያት የማታለል ሃያል አለው፡፡ ሰው ሲሸወድ እየተታለሉ ነው አይልም፡፡ ሰው ሲታለን ልባም የሆነ ጠቢብ የሆነ አራዳ የሆነ ይመስለዋል፡
ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ ወደ ዕብራውያን 3፡13
ሰው ግን እነዚህ ነገሮች ካላደረገ ልባም የሆነ አይምስለው፡፡ ይህን ነገሮችን የማያደርግ ሰው በራሱ አስተያየት ጠቢብ የሆነ ቢመስለውም ተሞኝቷል፡
1.      በአንድ ሃሳብ ለመስማማት ለአንድነት የማይሰራ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው
ለአንድነት ግድ የሌለው ሰው ተታሏል፡፡ ለአንድነት የማይሰራና ለግሉ የሚሰራ ሰው ልባም የሆነ ሊመስለው ይችላል ግን ስቷል፡፡
በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡2-3
2.     የትእቢትን ነገር የሚያስብ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው
ትእቢት ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛን ይቃወማል፡፡ ትእቢት ከሰይጣን ነው፡፡ እኔ ብቻዬን እችላለሁ እኔ ከሁሉም እበልጣለሁ የሚል የትእቢት ሃሳብን የሚያስብ ሰው የእግዚአብሄርን ሳይሆን የሰይጣን ሃሳብ እያሰበ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡3
3.     የትህትናን ነገር ለመስራት የማይተጋ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው
ከባልንጀራው እንደሚሻል እና ከሁሉም የተሻለ አክብሮት እና ጥቅም እንደሚገባው የሚያስብ ሰው ልባም የሆነ አይምሰለው፡፡ ባልንጀራውን ከእርሱ ይልቅ እንደሚሻል አስቦ በትህትና የማይቆጥር ሰው ለእግዚአብሄር መንግስት እንቅፋት ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3
4.     ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው  
ሰው እግዚአብሄር ካደረገው ከፍታ በላይ ከፍ ሊል አይችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ከሰጠው ከፍታ በላይ ራሱን ከፍ ሊያደርግ ከሞከረ ከዚያ ሌላ ደረጃ በላይ ስለሌለ ራሱን ዝቅ ያደርጋል ያዋርዳል እንጂ አያከብርም፡፡ እግዚአብሄርን የማይጠብቅና እግዚአብሄር ያልሰጠውን ቦታ ተንጠራርቶ በራሱ እጅ የሚወስድ ሰው የእግዚአብሄርን መንግስት አሰራር ያልተረዳ እውቀት የጎደለው ሰው ነው፡ 
ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል። የሉቃስ ወንጌል 14፡11
5.     ሳይሰስት ጥቅሙን ሳያስብ በእግዚአብሄር መንግስት ላይ ለመዝራት የሚሳሳ ሰው ልባም የሆነ አይምሰለው
እግዚአብሄር አገልግሉ ስጡ የሚለው ሊሰጠን ሊያበዛን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠውን ስጦታ በስስት የሚቀብር ንፉግ ሰው ልባም የሆነ አይምሰለው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። የማቴዎስ ወንጌል 25፡24-25
6.     በጥላቻ የሚመላለስ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው 
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ ሰው የተሰራው የእግዚአብሄርን ፍቅር በመቀበል በፍቅር እንዲኖር ነው፡፡ ምንም ምክንያት ቢኖረውም ከፍቅር ውጭ ማንኛውንም ሰውን የሚጠላ ሰው ጠቢብ የሆነ ከመሰለው ተሳስቷል፡፡
እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡14-15
7.      በእምነት የማይኖር ሰው በማየት የሚመላስ ሰው ልባም የሆነ አይምስለው 
ካለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ካለ እምነት ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት አይቻልም፡፡ ካለ እምነት ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ መስራት አይቻልም፡፡ ካለ እምነት ትርጉም ያለው ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ ሰው ግን በእግዚአብሄር ላይ እንዳይደገፍ ሁሉንም ነገር አሁን ማወቅ ከፈለገ ልባም የሆነ አይምሰለው፡፡ ሰው ግን በእግዚአብሄር ላይ እንዳይደገፍ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አሁን ማግኘት ከፈለገ ልባም የሆነ አይምሰለው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ላይ እንዳይደገፍ ሁሉንም ነገር አሁን ሊሆን ከፈለገ ልባም የሆነ አይምሰለው፡፡
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡6-7
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥበብ #ማስተዋል #መረዳት #ፍቅር #ጥላቻ #ትህትና #ትእቢት #አንድነት #አገልግሎት #እምነት #ቤተክርስትያን #መንፈስቅዱስ #ብርታት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment