Popular Posts

Thursday, August 2, 2018

በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ ፡ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ

ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡24፣27
ያለበትን ደረጃ የሚንቅ ሰው ሁል ጊዜ ሌላ ነገር የሚያምረው ሰው አንድ ያልገባው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ያለበትን ደረጃ የማያከብር ሰው ነገር ግን ለሌለበት ደረጃ ከመጠን በላይ የሚጓጓ ሰው አንድ ያልተረዳው እውነት አለ ማለት ነው፡፡
የሰው ደስታ እና እርካታ ያለው በእግዚአብሄር ውስጥ እንጂ በነገሮች ውስጥ አይደለም፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር እንጂ ነገር እንደ እግዚአብሄር በሌላ በምንም እንዳይረካ ተደርጎ ነው፡፡
እንዳገኘው ያለበትን ደረጃ የሚንቅና ሌላን ደረጃ የሚመኝ ሰው ያልተረዳው እውነት አለ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ውጭ በነገሮች ውስጥ ሰላምን ደስታንና እርካታን ሲፈልግ ይሰናከላል፡፡
ነገሮች ሰውን እንደ እግዚአብሄር ሊያስደስቱ አይችሉም፡፡ በእግዚአብሄር የተደሰተ ሰው ደግሞ ሌላ ነገር እንደ እግዚአብሄር ሊያስደስተው አይችልም፡፡  
ለአንድ ነገር ከመጠን በላይ የሚጓጓ ሰው የሚጓጓለትን ነገር በትክክል ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ የአንድን ነገር ጥቅሙን ብቻ አይቶ በጣም የሚጓጓ ሰው ካያችሁ ያ ሰው የነገሩን ሃላፊነት በውል እንዳልተረዳ በሙሉ ልባችሁ ትስማማላችሁ፡፡
እያንዳንዱ የህይወት ደረጃ የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ጥቅም የሌለው ነገር የለም፡፡ አለማግባት የራሱ ጥቅም አለው፡፡ አለማግባት የራሱ የሆነ ሃላፊነትም አለው፡፡ አለማግባት የራሱ የሆነ ተግዳሮት አለው፡፡ ማግባት የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ማግባት ደግሞ አለማግባት የሌሉበት የራሱ የሆኑ ሃላፊነቶችና ተግዳሮቶች አሉት፡፡
ሰው በሃይሉ አይበረታም፡፡ ማግባትም አለማግባትም በራስ የሚቻል አይደለም፡፡ አለማግባት የራሱ የሆነ የእግዚአብሄር ፀጋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ማግባትም የእግዚአብሄር ፀጋ ያስፈልገዋል፡፡
ኢየሱስ ስለማግባት ሲናገር ደቀመዛሙርቱ የማግባት ወግ እንደዚህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል ሲሉ ኢየሱስ ይህ ለተሰጣቸው ብቻ ነው በማለት ለማግባትም ላላማግባትም የእግዚአብሄር ፀጋ እንደሚያስፈልግ ያሳያል፡፡ ይህ የሚቻለው በራስ ፍላጎት ሳይሆን የእግዚአብሄር ፀጋ ለተሰጠው ሰው ብቻ ነው፡፡ ሰው ከማግባቱ በፊት የሚረዳው ፀጋ አለ ፣ ያለማግባት ፀጋ አለ እንዲሁም የማግባት ፀጋ አለ፡፡
ደቀ መዛሙርቱም፦ የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን፦ ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ የማቴዎስ ወንጌል 19፡10-11
ለምሳሌ ለማግባት በጣም የሚጓጓ ሰው ካያችሁ የትዳርን የሃላፊነት ጎን ያልተረዳ ሰው እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ለማግባት በጣም የሚጓጓ ሰው ባላገባበት ጊዜ የተሰጠውን ፀጋ እንደሚገባው አላከበረውም ማለት ነው፡፡  ማግባትም አላግባትም በእግዚአብሄር እርዳታ እንደሆነ የሚረዳ ሰው ለማግባት አይቸኩልም፡፡ ማግባትም አላግባትም በእግዚአብሄር እርዳታ እንደሆነ የሚረዳ ሰው በህይወቱ የሚሰራውን የእግዚአብሄርን ፀጋ ያከብራል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡24፣27
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #መፋታት#አንድስጋ #እውነት #ያጣመረውን #አንድስጋ #አይለየው #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment