Popular Posts

Tuesday, August 28, 2018

የቅዱሳን ህብረት ለማካፈል ለመባረክና ለመጥቀም

የቅዱሳን ህብረት በክርስትና ህይወት በጣም ወሳኝ የሆነ ስርአት ነው፡፡ የክርስትና ህይወታችን በሚገባ እንዲገነባና እንዲያድግ የቅዱሳን ህብረት የሚያበረክትው አስተዋኝኦ በቀላ የሚገመት አይደለም፡፡ እንዲያውም ለተሟላ ፍሬያማ የክርስትና ህይወት የቅዱሳን ህብረት ወሳኝ ነው፡፡
በአሁኑ ዘመን ከማህበራዊ መገናኛዎች መስፋፋት አንፃር ብዙ ሰዎች የተለያዩ መንፈሳዊ ጥቅሞችን በማህበራዊ መገናኛዎች እየተጠቀሙ ነው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ወንጌልን ለመስበክና የእግዚአብሄር ቃል ለማስፋት በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነው፡፡
የማህበራዊ መገናኛን ግን በትክክል አለመጠቀም በክርስትና ህይወታችን ላይ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ከአቅማቸው በላይ ማጋነና የሌላቸውን ነገር እንዲሰጡን መጠበቅ መንፈሳዊ ህይወታችንን የማቀጨጭ አደጋ አለው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ የቅዱሳን ህብረትን አይተካም፡፡ የማህበራዊ መገናኛ የቅዱሳን ህብረት ተጨማሪ ነገር እንጂ የቅዱሳንን ህብረት ሙሉ ለሙሉ የሚተካ ነገር አይደለም፡፡
ብዙ ሰዎች ቤተክርስትያን ላለመሄድ ምክኒያት የሚያገኙት ከቴሌቪዝን ከማህበራዊ መገናኛ እንደፌስቡክ ትዊተር እና ዩቱብ ባሉ መገናኛዎች ለመጠቀም እሞክራለሁ በማለት ነው፡፡
ስለ ማህበራዊ መገናኛዎች እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡ ብዙ ሰዎች ስለጌታ ኢየሱስ አዳኝነት በማህበራዊ መገናኛዎች እየሰሙ ነው፡፡ በማህበራዊ መገናኛዎች ዘዴዎችም አምልኮና የእግዚአብሄር ቃል ትምህርት ሰምተው የሚፅናኑና የሚታነፁ ሰዎች አሉ፡፡
ነገር ግን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሉና ከቅዱሳን ጋር ህብረትን ማድረግ አያስፈልግም የሚል አመለካከት ስህተት ነው፡፡ በማህበራዉ መገናኛዎች የማናገኛቸው ትምህርትና አምልኮዎች አሉ፡፡ በቤተክርስትያን ከቅዱሳን ጋር ህብረት የምናደርገው ከእግዚአብሄርን ለመጠቀም እና ለመቀበል ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ክርስትያን የምንሄደው ለመስጠትም ነው፡፡
ወደ ቤተክርስትያን ህብረት የምንሄደው ለቅዱሳን ህብረት ትብብርን ለመስጠት ነው፡፡ የቅዱሳን ህብረት ቤተሰባችን ነው፡፡ የቤተሰቡ ጥንካሬ የሚለካው በቤተሰቡ አባላት መሰጠት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ወደቤተክርስትያን የምንሄደው ለሌላው ወድማችን መፅናናት መታነፅና መበረታታ ምክኒያት ለመሆን ነው፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡24-25
ቤተክርስትያን የምንሄደው በህብረት አምልኮን ለመስጠት ነው
ቤተክርስትያን የምንሄደው በህብረት አምልኮን ለጌታ ለመስጠት ነው፡፡ የትኛውም የግል አምልኳችን የህብረቱ አምልኳችንን አይተካም፡፡ እግዚአብሄር እርሱን የምንፈራና የምናመልክ ሁላችን በህብረት ሆነን ስናመልከው ማየት ይፈልጋል፡፡
የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ። ትንቢተ ሚልክያስ 3፡16
ቤተክርስትያን የምንሄደው ጊዜያችንን ለመስጠት ነው
ቤተክርስቲያን ቤታችን ነው፡፡ ቤተክርስትያን ቤተሰባችን ነው፡፡ ቤተክርስትያን ካሸነፈች ቤታችን አሸነፈ፡፡ ጊዜያችን ጉልበታችን እውቀታችን ሁሉ ከእግዚአብሄር በአደራ የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ደጋግ መጋቢዎችና እንደ እግዚአብሄር ስጦታ አስተዳሪዎች በሁለንተናችን ቤተክርስቲያንን ለመደገፍ ራሳችንን እንሰጣለን፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡1-3
ቤተክርስትያን የምንሄደው ቃላችንን ለመስጠት ነው
ቤተክርስትያን የምንሄደው ወንድማችንን እና እህታችንን በቃል ለማፅናናትና ለማፅናት ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው እኛን ሲያዩን የሚፅናኑ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው በቃላችን ፀጋን የሚካፈሉ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር በፀጋ ባሳደገን መጠን በቃል አማካኝነት ፀጋን የሚያስችል ሃይልን ለሌሎች እናካፍላለን፡፡
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡29
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ማበረታቻ ለመስጠት ነው
ቤተክርስቲያን ቤተሰብ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ልጆች እንዳሉ ሁሉ በቤተክርስቲና እንዲሁ የተለያየ የእድገት ደረጃ ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ በቤተሰብ ትልቁ ትንሹን እየረዳ ለእድገቱ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ሁሉ በቤተክርስቲያን አንዱ ለአንዱ ያስፈልገዋል፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው ታናናሾቻችንን ለመንከናከብ እና ከታላለቆቻችን እንክብካቤ ለማግኘትና ለመማር ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው የታላላቆቻችንን ምሳሌነት ለመከተልና ለታናናሾቻችን ለክርስትና ህይወት ምሳሌ ለመሆን ነው፡፡፡
አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡10
ቤተክርስትያን የምንሄደው በፀጋ ስጦታችን ቅዱሳንን ለማገልገል ነው
ስንሰበሰንብ እግዚአብሄር በእኛ ተጠቅሞ ሌሎችን ያንፃል በሌሎች ተጠቅሞ እኛን ያነፀናል፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡26
ቤተክርስትያን የምንሄደው በጋራ እና በአንድነት የስምምነት ፀሎት ለመፀለይ ነው
የግል ጸሎት አለ የህብረት ፀሎት አለ፡፡ የግል ፀሎት የሚሰራው ስራ አለ የህብረት ፀሎት ደግሞ የሚሰራው ስራ አለ፡፡ የህብረት ፀሎት ተጠቃሚ ለመሆን በህብረት መስብሰብ ወሳኝ ነው፡፡
ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19-20
ቤተክርስትያን የምንሄደው ለሽማግሌዎች ህይወታችንን ለማሳየት ነው
የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች እና መጋቢዎች ለነፍሳችን የሚተጉ የእግዚአብሄር ስጦታዎች ናቸው፡፡
ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ወደ ዕብራውያን 13፡17
ወደ ቤተክርስቲያን ህብረት የምንሄደው ወንድሞቻችን በህይወታችን ችግር ካዩ እንዲወቅሱንና እንዲያስተካክሉን ህይወታችንን ለማሳየትና ግልፅ ለማድረግ ነው፡፡ ሰውን የምንበድለው አብረን ስንኖር ነው፡፡ ራስ ወዳድነታችን የሚገለጠው የክርስትናን ህይወት ደረጃ የሚያውቁ ቅዱሳን ጋር አብረን ስንኖር ህይወታችንን ሲያዩ ነው፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን የሚታየውና የምንወቀሰው የእግዚአብሄርን ቃል በሚያውቁ ቅዱሳን መካከል ስንኖር አስተሳሰባችንነ ንግግራችንና ድርጊታችን ሲያዩ ነው፡፡ የተበደለ የሚወቅሰን እና የሚያስተካከልን አብርን ስንኖር ነው፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። የማቴዎስ ወንጌል 18፡15-17
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ለህብረቱ የሚያመጣውን የጊዜውን ቃል ለመካፈል ነው
ምንም አይነት መንፈሳዊ እወቀት ቢኖረን ለህብረቱ ለዚያ ሳምንት አግዚአብሄር የሚልከውን የጊዜውን ቃል የምናገኘው ከቅዱሳን ህብረት ነው፡፡
የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ 25፡11
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ለቅዱሳንና ለሽማግሌዎች ህይወታችንን ለማሳየት ነው
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙረ ዳዊት 133፡1-3
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment