Popular Posts

Friday, August 17, 2018

ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?

ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ወደ ዕብራውያን 9፡14
ሰው ከሃጢያቱ ንስሃ ሲገባ እግዚአብሄር ከመቀፅበት ይቀበለዋል፡፡ ሰው ኢየሱስን እንደ አዳኙ በተቀበለ ቅፅበት የእግዚአብሄር ልጅ ይሆናል፡፡ ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን ሲቀበል ሃጢያት እንዳልሰራ ተደርጎ በእግዚአብሄር ይቅር ይባላል ሙሉ ተቀባይነትም ያገኛል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ማንኛውም ሰው በክርስቶስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ይሆናል፡፡
እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡21
ነገር ግን እግዚአብሄር ሰውን ይቅር ቢለውንም ሰው ግን ራሱን ይቅር ለማለት ጊዜ ይወስድበታል፡፡ እግዚአብሄር ቢቀበለውም ሰው እግዚአብሄር የተቀበለውን ፍፁም መቀበል ለመረዳት ጊዜ ይወስድበታል፡፡
እርሱ ብቻ አይደለም፡፡ ሰው በሃጢያት ህሊና ስለሚሰቃይ ብዙ ጊዜ ንስሃ የሚገባበት ነገር እግዚአብሄር ንስሃ እንዲገባበት የማይፈልገውን ነገር ሁሉ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ያላለውን በራሱ አነሳሽነት ራሱን ይወቅሳል፡፡ ሰው ራሱን በራሱ ይኮንናል፡፡
ሰው ከሃጢያቱ በላይ የሃጢያት አስተሳሰቡ ከእግዚአብሄር ይለየዋል፡፡ ሰው ሃጢያት ሰርቶ ይቅር እንደተባለ ከዚያ በኋላ ከእግዚአብሄር የሚያሸሸው የራሱ ህሊና እንጂ እግዚአብሄር አይደለም፡፡ ሰው በሃጢያቱ ንስሃ ገብቶ ከተመለሰ ደግሞ የሚወቅሰው የሞተ ህሊና እንጂ እግዚአብሄር አይደለም፡፡
ሰው ከሞተ ህሊና ነጻ ሲወጣ ወደኋላ ከሚጎትትው ነገር ሁሉ ተላቆ ለእግዚአብሄር መንግስት መሮጥ ይችላል፡፡ ሰው ግን የሞተ ስራ ህሊና ካልነፃ ለእግዚአብሄር መንግስት የማይጠቅም ይሆናል፡፡
እኔ በበኩሌ ስለ አንድ ነገር በህይወቴ የወቀሳ ስሜት ሲሰማኝ ፈጥኜ ንስሃ አልገባም፡፡ ንስሃ የአስተሳሰብና የመንገድ መለወጥ እንጂ የከንፈር ንግግር ብቻ አይደለም፡፡ ንስሃ የህይወት መንገድ መለወጥ እንደመሆኑ መጠን አጥብቄ ባልተረዳሁት ነገር ንስሃ ለመግባት አልፈጥንም፡፡ ንስሃ መግባት መልሼ አላደርገውም ማለት ስለሆነ መጀመሪያ ንስሃ የምገባው ለምን እንደሆነ ማጣራት እፈልፈጋለሁ፡፡ የስህተተኝነት ስሜት ስለተሰማኝ ብቻ ሳይሆን ስህተት መሆኑን በደንብ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ይህ ስህተት መሆኑን አሳየኝ ንስሃ እግባለሁ ደግሜም አላደርገውም ብዬ ቃል ለመግባት ንስሃ የምገባው ለምን እንደሆነ ማወቅ አለብኝ፡፡  
ስለአንድ ነገር የወቀሳ ስሜት ስልተሰማኝ ብቻ ንስሃ ገባሁ ብልና ደግሜ እንደማላደርገው ባልወሰን ንስሃ መግባት አይጠቅምም፡፡
እግዚአብሄርን እንደሚገባ ለማምለክ ህያው ህሊና ይጠይቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደሚገባን ለመገናኘት ህሊናችን ሊነፃ ያስፈልገዋል፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻል፡፡
ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ወደ ዕብራውያን 9፡14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #ኢየሱስ #ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #ሕሊና #ደም #አምልኮ #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መንገድንመቀየር #አስተሳሰብንመቀየር #መለወጥ #በረከት #መታደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment