Popular Posts

Saturday, August 4, 2018

መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል

መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። መጽሐፈ ምሳሌ 18፡1
በህይወታችንና በአገልግሎታችን አንድ ትርጉም ያለው ነገር ለማድረግ መተባበርን ይጠይቃል፡፡ እኛ በራሳችን ውስን ነን፡፡ የሁሉም ችግር መፍትሄ በአንድ ሰው ውስጥ የለም፡፡ ሰው በበዛ ቁጥር መፍትሄ ይበዛል፡፡ ከእኛ ከፍ ያለ ነገር ለማድረግ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በአንድነት የሚሰራው ስራ ውጤት ለብቻ ከሚሰራው ስራ ውጤት እጅግ ይበልጣል፡፡
እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥ እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር? ኦሪት ዘዳግም 32፡30
አንድነት መልካም ነው
አንድነት እግዚአብሄርን ያከብራል፡፡ መለያየት እግዚአብሄርንና ሰውን ያስነውራል፡፡ መለያየት የሰውን ሃይል ያዳክማል፡፡ መለያየት አቅምን ይበታትናል፡፡
ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። የዮሐንስ ወንጌል 17፡20-21
አንድነት ጥበብን ይጠይቃል
አንድነት መልካም ቢሆንም ነገር ግን አንድነትን ማምጣት ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ አንድነት የቸልተኞች አይደለም፡፡ አንድነት የትእቢተኞች አይደለም፡፡ አንድነት ትህትናን ይጠይቃል፡፡ አንድነት ትጋትን ይጠይቃል፡፡ አንድነት መስዋእትነትን ይጠይቃል፡፡ አንድነት መተውን ይጠይቃል፡፡ አንድነት እምነትን ይጠይቃል፡፡ አንድነት መዋረድን ይጠይቃል፡፡  
በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡2-3
ሰው የግል ምኞት ከሌለው በአንድነት መስራትንና በአንድነት መባረክን ይመርጣል፡፡ ሰው የግል ምኞት ካለው ግን የግል ምኞቱን በአንድነት መፈፀም ስለማይችል መለየትን ይፈልጋል፡፡ ሰው የግል ምኞቱንም ለማሳካት ፈልጎም አንድነትን ፈልጎም አይሆንም፡፡ አንድነት ለጋራ ጥቅም ነው፡፡ የግል ጥቅምን በአንድነት መስራት ስለማይቻል የግል ጥቅሙ የበለጠበት ሰው ይለያል፡፡  
ካልተባበርን እናንሳለን፡፡ በአንድ ሃሳብ ስር ካልተባበረን እንደክማለን፡፡
ስለዚህ ነው መለየትን የሚወድ ሰው ምኞቱን የሚከተል ሰው ነው፡፡ ምኞቱን የሚከተል ሰው የአንድነትን ፍሬ ይንቃል፡፡ ምኞቱን የሚከተል ሰው ከአንድነት ጥቅም ይልቅ መለየት ይበልጥበታል፡፡ መለየትን የሚከተል ሰው ደግሞ የአንድነትን ጥበብ ይቃወማል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። መጽሐፈ ምሳሌ 18፡1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #መለየት #ምኞት #ጥበብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment