Popular Posts

Follow by Email

Saturday, August 25, 2018

የሌለኝ ነገር የሌለኝ ስለማያስፈልገኝ ነው

ዴቪድ ኦዬዴፖ የተባሉ የእግዚአብሄር ሰው እንዲህ ይላሉ የሌለኝ ነገር የመያስፈልገኝ ነው፡፡
ከባድ አባባል ነው ነገር ግን እውነተኛ አባባል ነው፡፡ እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣዕኝ የለም ብለን ካመንን በግልባጩ ያጣነው ነገር ስለማያስፈልገን ነው ብለን ማመን አለብን፡፡
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙረ ዳዊት 23፡1
በሌላ አነጋገር አሁን ያለኝ ማንኛውም ነገር አሁን ላለሁበት ደረጃ ይበቃል ማለት ነው፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6
አሁን ያለኝ ነገር እግዚአብሄር ለጠራኝ ጥሪ በቂ ነው፡፡ እግዚአብሄ ለህይወትና እርሱን ለመምሰል የያስፈልግውን ነገር ሁሉ ሰጥቶኛል፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3
1.      ያለሁበት መንፈሳዊ ደረጃ ይበቃል
በመንፈሳዊ ህይወት በጣም ማደግ ከመፈለጋችን የተነሳ ብዙ ጊዜ አሁን ያለንበትን መንፈሳዊ ደረጃ እድገት አንመለከትም፡፡ ወደፊት በምንደርስበት መንፈሳ ደረጃ ሃሳብ ስለተያዝን አሁን ስላለንበትን መንፈሳዊ ደረጃ እድገት እግዚአብሄርን አናመሰግንም፡፡ ደፊት ከምንደርስበት መንፈሳዊ ደረጃ ትልቅነት አንፃር አሁን ያለንበት የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ በቂ ነው ብለን አናስብም፡፡ አሁን ያለንበትን መንፈሳዊ ደረጃ ለመድረስ ከምንፈልግበት መንፈሳዊ ደራጃ እንፃር ስለምናየው ያንስብናል፡፡
እውነት ነው ልንደርስበት ካለው መንፈሳዊ ደረጃ አንፃር ይህ ያለንበት ደረጃ ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ከመጣንበት መንፈሳዊ ደረጃ አንፃር አሁን ያለንበት መንፈሳዊ ደረጃ ትልቅ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሄር አሁን ከሰጠን የህይወት አላማ አንፃር ያለንበት የህይወት ደረጃ በቂ ነው፡፡ የሚያስፈልገን አሁን ያለንበትን  መንፈሳዊ ደረጃ አክብረን ለእግዚአብሄርን መንግስት መሮጥ ነው፡፡ አሁን ላለን መንፈሳዊ ሃላፊነት ያለንበት መንፋሳዊ ደረጃ ብቁ ነው፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3
2.     ያለሁበት የገንዘብ ደረጃ ይበቃል
እግዚአብሄር ገንዘብን የሚሰጠን በፍላጎታችን መጠን ነው፡፡ እግዚአብሄር ገንዘብን የሚሰጠን በፈለግነው መጠን ግን አይደለም፡፡ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሁሉ አድርገን የፈለግነው ያህል ገንዘብ ወደ እኛ ካልመጣ የፈለግነው ገንዘብ አያስፈልገንም ማለት ነው ብለን ማመን አለብን፡፡ ሁለት አንድ አይነት ስራ የሚሰሩ ሰዎች የተለያየ ገንዘብ የሚክፍሉዋቸው የተለያየ ደንበኛ ወደ እነርሱ ሊመጣ ይችላል፡፡ ብዙ የወጪ ፍላጎት ያለበት ሰው ብዙ ገንዘብ ወደ እርሱ ይመጣል ብዙ የወጪ ፍላጎት የሌለበት ሰው ደግሞ ብዙ ገንዘብ ወደ እርሱ ላይመጣ ይችላል፡፡ ገንዘብ ወጪ መሸፈኛ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ወደ እኛ ካልመጣ እግዚአብሄር ይመስገን ብዙ ወጪ የለብንም ማለት ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ወደ እኛ መጥቶም ብዙ ወጪ መሸፈንና ትንሽ ገንዘብ ወደ እኛ መጥቶ ትንሽ ወጪ መሸፈን አንድ ነው፡፡ በአንዳንድ ወር ተረፍ ያለ ገንዘብ ወደ እኛ ሲመጣ ተጨማሪ ወጪ እየመጣ ነው ማለት ነው ብለን ማሰብ አለብን፡፡ በሰው ወጪ ብዛት መቅናት እንደማንፈልግ ሁሉ በሰው የገቢ ብዛት አንቅና፡፡  
የሰው ዋናው ችግር የገንዘብ እጥረት ሳይሆን ያለኝ የሰው ዋናው ችግር ያለኝ ይበቃኛል ብሎ በእምነት የመኖር የድፍረት ችግር ነው፡፡
አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ ስለዚህ በድፍረት፦ ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን። ወደ ዕብራውያን 13፡5-6
3.     ያለሁበት የእውቀትና የጥበብ ደረጃ ይበቃል
ልጆቼን ምን አይነት ትምህርት ቤት ማስተማር አለብኝ? ልጆቼ ከክፍል ስንተኛ ደረጃ ቢወጡ ነው የተሳካ ህይወት የሚኖራቸው ብለን እናስባልን፡፡ መክፈል የምችለውን የትምህርት ቤት ክፍያ መጠን ብቻ ከከፈልን በኋላ ለልጆቻችን የወደፊት ህይወት መሳካት በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ወሳኝ ነው፡፡ ለልጆቻችን የወደፊት ህይወት መሳካት በገንዘብ አቅማችን መክፈል የምንችልበት ትምህርት ቤት ይበቃል፡፡ መክፈል ከምችለው ደረጃ በላይ ለመክፈል ሳንጨነቅ እግዚአብሄር የልጆቻችንን ወደፊት እንደሚባርክ ማመን ያስፈልጋል፡፡  
የሰው የትምህርት አቀባበል እንደየሰዉ የተለያየ ነው፡፡ ልጆች ለትምህርታችው ትኩረት እንዲሰጡ እንዲሁም ልጆች በሚቸገሩበት የትምህርት መስክ እርዳታን እንዲያገኘየ ከረዳናቸው በኋላ ያላቸው የትምህርት ችሎታ በቂ እንደሆነ ማመን አለብን፡፡ ሰነፍ ካልሆኑና በትጋት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ከሆነ ያላቸው የእውቀት ደረጃ እግዚአብሄር በህይወታችው ላለው አላማ በቂ እንደሆነ በማመን ማረፍ አለብን፡፡  የተለየ የህይወት አላማና ተፈጥሮአዊ የትምህርት ብቃት ካላቸው ልጆች ጋር ልጆቻችንን እያስተያየን መኮነን ይጎዳቸዋል እንጂ አይጠቅማቸውም፡፡ አንዳንድ ትጉህ ተማሪ ካለው የትምህርት አያያዝ ተፈጥሮ አንፃር ከክፈሉ 10ኛ ከወጣ መሸለም አለበት፡፡ እንዳንዱ ሰንፍ ተማሪ ከክፍሉ 3ኛ ከወጣ መወቀስ አለበት፡፡ በነገር ግን በትጋት አጥንቶና ለፍቶ 10 የወጣው ተማሪ ለተፈጠረበት አላማ ያለው አወቀት በቂ ነው፡፡   
የሰውን ወደፊት የሚያስተካክልው እግዚአብሄር እንጂ ጥበብ ወይም እውቀት አይደለም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24
በምናልፍበት ሁኔታ እግዚአብሄር ጥበብ እንዲሰጠን ከጠየቅን በኋላ ለጊዜው የሚበቃን ጥበብ እንዳለን አውቀን በእምነት እና በድፍረት እንድንኖር እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡5-6
4.     ያለሁበት የእምነት ደረጃ ይበቃል
ሰው ብዙ ጊዜ መጨመር የተሻለ ትልቅ ነገርን ይፈልጋል፡፡ አንዳንድ ሰው የተሻለ ትልቅ ተጨማሪ ነገር ሁልጊዜ ትክክል ይመስለዋል፡፡ ሰው ሁልጊዜ ትልቅ ተጨማሪ የተሻለ ነገር ሲፈልግ ዛሬን መኖር ይረሳል፡፡ ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን እምነት ጨምርልን አሉት፡፡ ኢየሱስ ያላቸው ያለችሁን እምነት  ከተጠቀማችሁ እግዚአብሄር አሁን በህይወታቸሁ ሊሰራ ላለው አላማ በቂ ነው፡፡ ህይወታችሁን ለመለወጥ ያላችሁ እምነት ይበቃል፡፡ ጥያቄው የመጨመር ሳይሆን የመጠቀም ነው እያላቸው ነው፡፡   
ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 17፡5-6
የእግዚአብሄርን ቃል በቀጣይነት በመስማት እምነት ሲመጣልን ደግሞ አሁን ላይ ቆም ነገን ስናየው ተራራ የሆነብን ነገር በነገ እምነት ደልዳላ ሜዳ ይሆናል፡፡ 
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡34
የዛሬ እምነታችን ለነገ ስራ አይበቃም እንጂ ለዛሬ ስራ አያንስም፡፡ የዛሬ እምነታችን የሚበቃው ለዛሬ ስራ እንጂ ለነገ ተግዳሮታችን አይደለም፡፡ የዛሬው እምነታችን ለዛሬው ስራ ግን በምንም መልኩ አያንስም፡፡
የሚያስፈልገን እምነት በጊዜው ይመጣል፡፡
እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ወደ ገላትያ ሰዎች 3፡25
5.     ያለሁበት የእርምጃ ደረጃ
እግዚአብሄርን የሚቀድመው ሰው እንደሌለ ሁሉ ከእግዚአብሄር ጋር የሚራመድን ሰው የሚቀድመው ሰው የለም፡፡ የእግዚአብሄርን ድምፅ ከፈለግና ከታዘዝን ማንም ሰው በህይወታችን ሊቀድመን አይችልም፡፡ እግዚአብሄርን እየተከተልን ያለንበት የእርምጃ ደረጃ በቂ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለጠራን ጥሪ የተጓዝነው የጉዞ ርቀት በቂ ነው፡፡ ያ ማለት ነገ ሌላ ርቀት ላይ መድረስ የለብንም ማለት ግን አይደለም፡፡ ለዛሬ ግን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መድረስ ላለብን የህይወት ግብ ያለንበት የእርምጃ ደረጃ የተጓዝነው ርቀት በቂ ነው፡፡ 
የእግዚአብሄርን ድምፅ እየሰማህ የምትሄድ ከሆነ የአንተ እርምጃ አልዘገየም አልፈጠነም፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ የመከተል እንጂ ለሌላ ስራ ከተጠራው ከሌላው ሰው ጋር የመሽቀዳደም ስራ አልተሰጠንም፡፡ እርምጃችንን ከሚመራን ጌታ እርምጃ ጋር እንጂ እኛ ከተጠራንበት የህይወት አላማ የተለየ ነገር ከተጠራው ሰው እርምጃ ጋር አናስተያይ፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና። ኦሪት ዘፍጥረት 5፡24
6.     ያለኝ መልክና የሰውነት አቋም በቂ ነው
ግሩምና ድንቅ ተደርጌ ተፈጥሬያለሁ፡፡ የሰው ሁሉ መልክና አቋም ይለያያል፡፡ የሰው መልኩ እንደ እጁ አሻራ የተለያየ ነው፡፡ ሰው የተጠራው ለተለያ የህይወት አላማ ነው፡፡ የሰው የህይወት አላማ ከሚጠይቀው መልክና ቀለምና ቁመና ጋር ተፈጥሮአል፡፡ የእያንዳንዱ ሰው መልክና ቁመና ለተፈጠረበት አላማ እግዚአብሄር በምድር ላይ ለአየለት ቀኖች አይበዛም አያንስም፡፡ የሌለኝ ቁመትና ቅላት የማያስፈልገኝ ነው፡፡
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። መዝሙረ ዳዊት 139፡14-16
7.     ያለህ ጉልበት በቂ ነው
ተጨማሪ ሃይል ከመፈልግ ይልቅ በሃይላችን ተጠምንን የፍቅርን ተግባር ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ አሁን ያለን ጉልበትና ሃይል እግዚአብሄር ለጠራን አላማ በቂ ነው፡፡ ጉልበት እንዳነሰን ድካም እንደሚሰማን ብናስብም እግዚአብሄር ለጠራን ስራ በቂ ጉልበት አለን፡፡ የሚያስፈልገን ተጨማሪ ጉልበት ሳይሆን ያለን ጉልበት ለተጠራንበት አላማ እንደሚበቃን ማመን ነው፡፡
ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡8-9
8.     ያለን ተሰሚነት በቂ ነው
ዝነኛ ለመሆንን ከመድከም የልቅ ያለንን ዝና ተጠቅመን ለሰዎች መልካም ማድረግ ፍሬያማ ያደርገናል፡፡ አሁን ያለን ተሰሚነትና ዝና እግዚአብሄር በአሁኑ ጊዜ ለሰጠን ሃላፊነት አያንስም፡፡ ነገ አገልግሎታችን ሲሰፋ እግዚአብሄር ራሱ ዝናችንን ያወጣዋል፡፡
ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። የማቴዎስ ወንጌል 4፡24
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እረኛ #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ዝና #ገንዘብ #እውቀት #ጥበብ #እድገት #መልክ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment