በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ
ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡1-4
በእምነት የደከመውን እግዚአብሄር ተቀብሎታልና
እናንተም ተቀበሉት፡፡
እግዚአብሄር የተቀበለውን የማንቀበልበት ምንም
ምክኒያት የለንም፡፡ እግዚአብሄር የተቀበለውን በመቀበላችን አንሳሳትም፡፡ እግዚአብሄር የተቀበለውን ባለመቀበል ግን በግልፅ እንስታለን፡፡
በመጀመሪያ እኛ ራሳችን እንደማንኛውም ፍጥረት
በእግዚአብሄር ተፈጠርን እንጂ ሌላውን አልፈጠርንም፡፡ እኛ ራሳችን እንደ ማንኛውም ሰው በጌታ ዳንን እንጂ ማንንም አላዳንም፡፡
ሁለተኛ ለእያንዳንዱ የሰጠውን የሚያውቅው እግዚአብሄር
እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ለእኛም የሰጠውን የሚያውቅ እግዚአብሄር እንጂ ሌላው ሰው አይደለም፡፡ እኛ በአንደ በኩል ድነን ከሆነ
እገዚአበሄር ይመስገን፡፡ ደህንነቱ የእኛ አይደለም፡፡ ደህንነቱ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ሌላው አልዳነም ብለን ካሰብን እንኳን
ልንደግፈው ልናዝንለት እንጂ ልንፈርድበት አይገባንም፡፡
ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ
የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡3-4
ስለዚህ እንዳልተቀበልነው መመካት አይገባንም፡፡
በእኛ ዘንድ ያለ ምንም አይነት በጎነት ቢኖር ከእግዚአብሄር የተቀበልነው ነው፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። የሉቃስ ወንጌል 12፡48
እኛ
እግዚአብሄር ስለሌላው ሎሌ ካልመራን በስተቀር ማንንም መኮነን አንችልም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል የምናምነውን መናገር እንችላለን፡፡
ነገር ግን እምነታችንን በሌላው ሎሌ ላይ መጫን ግን አንችልም፡፡ የእያንዳንዳችን የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ ይለያያል፡፡ ክርስትና
እንደ ቤተሰብ አባላት የተለያየ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ሁላችንም ወደ ፍፁምነት እንሄዳለን ስንሄድ እያንዳንዱ በደረሰበት
የእውቀት ደረጃ ይመላለሳል እንጂ አንድ ወጥ የእውቀት ደረጃ የለም፡፡
እንግዲህ
ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም
በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡15-16
ለእያንዳንዳችን
ጌታ ያሰመረልን መሮጫ መስመር አለ፡፡ እያንዳንዳችን የምንወቀሰው ከዚያ ከጥሪያችን እንጻር እንጂ ከሌላ ሰው ጥሪ አንፃር መሆን
የለበትም፡፡
ብቻ
ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት
ሁሉ እደነግጋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡17
እግዚአብሄር
የጠራው ለምን እንደሆነ ምን መንፈሳ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያይ እውነተኛም ፈራጅ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ሌላው
ላይ ሊፈርድ የሚችልው እግዚአብሄር ስለሌላው ሎሌ የገለጠለትና እንዲገስፀው የላከው ሰው ብቻ ነው፡፡
ማድረግ
የምንችለው አንድ ነገር እግዚአብሄር እንዲረዳው ለእግዚአብሄር ማሳወቅ እንዲሁም የደከመውን የምንረዳበትን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው፡፡
ማንም
ሰው ሰራተኛውን ሌላ ማንም እንዲፈርድበት እንደማይፈልግ ሁሉ እግዚአብሄርን ሰራተኛውን ማንም እንደ እርሱ ያለ ሰራተኛ እንዲፈርድበት
አይፈልግህም፡፡
ሰው
በሌላው ሰራተኛ ላይ መፍረድ ድንበርን መዝለል ነው፡፡ ሰው በሌላ ሰራተኛ ላይ መፍረድ ካለ ደረጃ አላግባብ ማንጠራራት ነው፡፡ ሰው
በሌላው ሰራተኛ ላይ መፍረድ የእግዚአብሄርን የፍርድ ወንበር መያዝ ነው፡፡
ለእግዚአብሄር
የማየጠቅም ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር የሳተውን እንዴት እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ያመፀበትን ስጋ እንዴት እንደሚቀጣው
ያውቃል፡፡
አገልጋዩ
ቢወድቅ መጀመሪያ ከማንም በላይ የሚጎዳው ተገልጋዩ እግዚአብሄር ነው፡፡ አገልጋይ ቢወድቅ ከማንም በላይ መጀመሪያ የሚያውቀው ተገልጋዩ
እግዚአብሄር ነው፡፡ አገልጋዩ ቢወድቅ መጀመሪያ ከማንም በፊት የሚያገባው ባለቤቱ እግዚአብሄር ነው፡፡
ስለ
እግዚአብሄር አገልጋይ ከእግዚአብሄር በላይ አናውቅም፡፡ ስለ እግዚአብሄር አገልጋይ ከእግዚአብሄር በላይ አንቀናም፡፡ ስለ እግዚአብሄር
አገልጋይ ከእግዚአበሄር በላይ መጨነቅ አይገባንም፡፡
ስለራሳችሁ
ህይወት ሀላፊነት ትወስዳላችሁ፡፡ ስለሌላው ህይወት ሃላፊነት ላለመውሰድ ግን መፍራት አለባችሁ፡፡ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ ጻድቁም
ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ እስከማለት ድረስ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍና ማረፍ አለባችሁ፡፡
ዓመፀኛው
ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥
ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። የዮሐንስ ራእይ 22፡11-12
እረፉ
ይላል አግዚአብሄር እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ፡፡ እግዚአብሄር በማንም ሰው አይረዳም፡፡ እግዚአብሄርን ልጆቹን ለማሳደግና ለመቅጣት
አትረዱትም፡፡
ስለዚህ፥
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ
አይሠራምና። የያዕቆብ መልእክት 1፡19-20
አቢይ
ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት
#የሚፈርድ #የሚያማ
#ወንጌል #መውደድ
#ፍቅር #የህይወትምስክርነት
#መታዘዝ #ማገልገል
#መውደድ #እውነት
#ትህትና #ትንሳኤ
#ህይወት #ወንጌል
#አማርኛ #ስብከት
#መዳን #መፅሃፍቅዱስ
#መንፈስቅዱስ
#ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment