Popular Posts

Tuesday, August 28, 2018

የአዲስ ዓመት ውሳኔ - ከቅዱሳን ጋር ይበልጥ ህብረትን ማድረግ

ሁልጊዜ አዲስ አመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ ይመጣል፡፡ አዲስ አመትን በእውነት አዲስ ለማድረግ ግን በህይወታችን የምንወስናቸውና የምንተገብራቸው ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡
በአዲሱ አመት መተው የሌለብንና እንዲያወም ይበልጥ ማድረግ ያለብን የቅዱሳን ህብረት ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ራሱን ለሰው አባት አድርጎ በመስጠት አላበቃም፡፡ ሰው አባት ብቻ ሳይሆን ወንድምና እህት አንደሚያስፈልገው እግዚአብሄር አውቋል፡፡ እግዚአብሄር ራሱን አባት አድርጎ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጉትን ወንድሞችና እህቶች ሰጠው፡፡
በወንድሞችና በእህቶች ህብረት የተቀመጠ ታላቅ በረከት አለ፡፡
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙረ ዳዊት 133፡1-3
በአዲሱ አመት ከቅዱሳን ህብረት የሚያዘናጋንን ማንኛውንም ነገር ለመተው መወሰን ብልህነት ነው፡፡ አንዳንዱ የህይወታችን ጥያቄ የሚመለሰው በቅዱሳን ህብረት ውስጥ ነው፡፡ በቅዱሳን ህብረት ውስጥ ያለውን ፀጋ የምንካፈለው በቅዱሳን ህብረት ነው፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳንን ባሳደገበት ፀጋ ተካፋይ የምንሆነው በህብረት ውሰጥ ነው፡፡ ካለንበት ነገር ሊያወጣን የሚያስችል የፀጋን ሃይል የምንካፈለው በቅዱሳን ውስጥ ነው፡፡
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡29
ቅዱሳን እርስ በእርሳችን የምንበረታታውና የምንፅናናው በቅዱሳን ህብረት ነው፡፡ ፍቅርና መልካም ስራ ትጋትና ክትትል የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ቅዱሳን እርስ በእርሳችን ለፍቅርና ለመልካም ስራ የምንነቃቃው በቅዱሳን ህብረት ውስጥ ነው፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡24-25
ጌታን ለማምለክ የእግዚአብሄርን ቃል ከቅዱሳን ጋር ለመካፈልና የእግዚአብሄርብ ፍቅር ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ለመረዳት ራሳችንን ለህብረት መስጠት ይጠይቃል፡፡
በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፡16-19
ለአገልግሎት ፍፁምና ሙሉ ሰው የሚያደርገንን የክርስቶስን እውቀት የሚያካፍሉ የአገልግሎት ስጦታ ያላቸው አገልጋዮች የተሰጡት ለቅዱሳን ህብረት ነው፡፡
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡11-13
ባለፈው አመት እግዚአብሄር ከሰጠን 365 ቀናት ውስጥ ምን ያህሉን ለቅዱሳን ህብረት እንደተጠቀምንበት እያንዳንዳችን እናውቃለን፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ግን የክርስቶስ መምጣን እየቀረበ መሆኑን እያያችሁ የቅዱሳንን ህብረት ይበልጥ አድርጉት እንደሚል ይበልጥ ለማድረግ መወሰን አለብን፡፡
በአዲሱ አመት የቅዱሳን ህብረትን ስናስብ ለመቀበልና ለመባረክ ብቻ ሳይሆን ለመጥቀም ፣ ለብዙዎች በረከት ለመሆንና ለማገልግል መወሰን ህይወታችንን ፍሬያማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡24-25
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment