Popular Posts

Thursday, August 2, 2018

የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽም

ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ አላወቅሽምና። የሉቃስ ወንጌል 19፡41-44
ኢየሱስን ማወቅና መለየት የጉብኝቶች ሁሉ ጉብኝት ነው፡፡ ኢየሱስበመድር ሲመላለስ ያለቀሰበት ምክንያት የእስራኤል ህዝብ የመጎብኘቱን ጊዜ ባለመለየቱ ነበር፡፡ ዘመኑ እስራኤል ሰላም የሚያስፈልጋት ወሳኝ ጊዜ ነበር፡፡ እንደዛን ጊዜ ሰላም የሚያስፈልጋት ጊዜ አልነበረም፡፡ ብትቀበለው በኢየሱስ የመጣው የሰላም ጉብኝት ከጠላቶችዋ የሚያሳርፋት መፍትሄ ነበር፡፡ እስራኤል ነገር ግን ለሰላምዋ የሚሆነውን ነገር አላወቀችም፡፡
እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 12፡32
እግዚአብሄር የእድል አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በጊዜው ብዙ እድሎችን ወደህይወታችን ያመጣል፡፡ መፅሃፍ ለሁሉ ጊዜ እንዳለው ይናገራል፡፡ ለመጠበቅ ጊዜ አለው የጠበቅነውንም ፍሬ ለማግኘት ጊዜ አለው፡፡ ጊዜን አለመለየት የጉብኝት ጊዜያችንን እንዳናውቅ ያደርጋል፡፡ ጊዜን አለመለየት የጉብኝት ጊዜያችንን በከንቱ እንድናሳልፍ እንቅፋት ይሆናል፡፡ ጊዜን አለማወቅ ለጠላት እንድንጋለጥ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን የሚልካቸውን እድሎች ነቅተን በጠበቅንና በተጠቀምናባቸው መጠን ህይወታችን ፍሬያማ ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር በየጊዜው ወደ እኛ የሚያመጣውን ጉብኝት በከንቱ ባሳለፍነው ቁጥር እንጎዳበታለን፡፡
የመጐብኛችንን ጊዜ ያለማወቅ ምክንያቶች 
1.      አለመንቃት
የፀሎታችን መልስ የሚመለስበት የጉብኝታችን ጊዜ መጥቶ ከጉብኝት ጊዜያችን ጋር የምንተላለፈው ባለመንቃት ነው፡፡ ካልነቃን ጉብኝታችንን አናይም ፣ ካልነቃን የጉብኝታችንን ድምፅ አንለይም ፣ ካልነቃን ጉብኝታችንን ለመቀበል እንዘጋጅም፡፡
ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡11-13
2.     በመጠን አለመኖር
ህይወት ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ህይወት በቸልታ የምንከናወንበት ሃላፊነት አይደለም፡፡ ለመንቃት በመጠን መኖር ይጠይቃል፡፡ በህይወት ለመንቃት ሁሉም በልክ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በህይወት ለመንቃት ህይወታችንን ቀለል ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ለመንቃት በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ማተኮር ይጠይቃል፡፡ ለመንቃት እንደወታደር የአላማ ሰው ቆፍጣናና ጨካኝ ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። 2 ወደ ጢሞቴዎስ 2፡1፣4
3.     በቃሉ ከባቢ ውስጥ አለመገኘት
እግዚአብሄር ጉብኝትን የሚያመጣው እንደቃሉ ነው፡፡ ቃሉን የምንፈልግ በቃሉ የምንተጋ ከሆንን የትኛውም የጉብኝት እድሎች በህይወታችን አያመልጡንም፡፡
የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡16-17
4.     እግዚአብሄር ባስቀመጠን ቦታ አለመቀመጥ
እግዚአብሄር ባሉበት ቦታ እንደሚደርሳቸውና ህይወታቸውን እንደሚለውጥ የማያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎች በጊዜው ፋሽን ወደሆነው ሰዎች ግር ወደሚሉበት ግር የሚሉትና ከጉብኝታቸው ጋር የሚተላለፉት ስለዚህ ነው፡፡ ሰዎች በትምንህርት ንፋስ የሚፍገመገሙት ስለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ፀንተው የእግዚአብሄርን ጉብኝት በቦታቸው ሆነው የማይብቁት ስለዚህ ነው፡፡ ሰዎች በሚታይ ነገር የሚፍገመገሙት ስለዚህ ነው፡፡
እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ የሉቃስ ወንጌል 2፡25-28
5.     ትልልቅ ነገርን መፈለግ
የእግዚአብሄር ነገር የሚገለጠው በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጉብኝት የሚመጣው በታላላቅ ነገሮች ውስጥ አይደለም፡፡ አንድ የእግዚአብሄር የጉብኝት ቃል ህይወታችንን ይለዋውጠዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ካከበርን ከእግዚአብሄር የጉብኝት ጊዜ ጋር እንገናኛለን፡፡ ነገር ግን ሁሌ የየእለት የእግዚአብሄር አሰራሮችን ንቀን የእግዚአብሄርን ጉብኝት በታላቅ ነገሮች ውስጥ ከፈለግን ከጉብኝታችን ጋር እንተላለፋለን፡፡
ኢየሱስ እንደቃሉ እንጂ ሰዎች በጠበቁት በነገስታት ቤት አልተወለደም፡፡ ኢየሱስ በቤተልሄም በግርግም ተወለደ፡፡ በእግዚአብሄር ቃል በትጋት የጠበቁት በነገስታት ቤት መካከል ያልጠበቁት የእግዚአብሄርን ጉብኝት ኢየሱስን ለዩት፡፡
ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። የሉቃስ ወንጌል 2፡36-38
6.     በእምነት አለመፅናት
ብዙ ሰዎች እምነት ያላቸው ይመስላቸዋል ነገር ግን እምነታቸንው ሲፀኑ አያሳይም፡፡ የእግዚአብሄር ጉብኝት በድንገት በእድል አይገኝም፡፡ የእግዚአብሄር ጉብኝት የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው፡፡
ቆይቼ እግዚአብሔር ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኽቴንም ሰማኝ። መዝሙረ ዳዊት 40፡1
እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? የሉቃስ ወንጌል 18፡8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መጐብኘትሽ #አላወቅሽም #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment